ምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ
ምክር ቤቱ ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 27፣ 2017 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛ ልዩ ስብሰባው ሁለት የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው ዘላቂና ሁሉ አቀፍ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ የብድሩን አስፈላጊነት እና አላማ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ አቅርበዋል፡፡
በብድር የተገኘው ገንዘብ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለመደገፍ እንዲቻል እና የፌደራል መንግሥትን የ2ዐ18 ዓ.ም በጀት በቀጥታ ለመደገፍ እንደሚውል ወ/ሮ መሰረት አስረድተው፣ ብድሩም ከወለድ ነጻ እና በረጅም ዓመታት የሚከፈል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤትም በብድር ስምምነቱ ላይ ተወያይቶ ስምምነቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
በተመሣሣይም፣ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለፍጥነት መንገድ ልማት ድጋፍ ፕሮጀክት (ሞጆ-ሀዋሳ መንገድ) ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አጽድቋል፡፡
በብድር የተገኘው ገንዘብ ሊጠናቀቅ የተቃረበውን የሞጆ-ሀዋሳ የፍጥነት መንገድ ሦስተኛ ክፍል ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እንደሚረዳ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም፣በብድሩ እየተከናዎኑ ያሉ የተለያዩ ስራዎች ያለችግር እንዲጠናቀቁ የሚያስችል መሆኑን ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱም በብድር ስምምነቱ ላይ ተወያይቶ ስምምነቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
በብድር የተገኘው ገንዘብ የ 2018 በጀትን ፋይናንስ ለማድርግ እና የተጀመሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አሕመድ ሽዴ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በናይጄሪያ መንግሥታት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ የሁለቱ አገር ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት የሚያስችለው ስምምነት መሆኑን ወ/ሮ መሰረት አብራርተዋል፡፡
ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና የፖለቲካ ትብብር ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱም በስምምነቱ ላይ ከተወያዬ በኋላ ስምምነቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives