በበጀት ዓመቱ የ8.4 በመቶ አጠቃላይ ዕድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ ይገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 11/2017 ዓ.ም፤ በኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የ8.4 በመቶ አጠቃላይ ዕድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የአፈፃፀምን መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
6ኛ ዙር የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የኢኮኖሚ ዘርፉን በሚመለከት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል፤ በአምራች ዘርፉ ያለውን የጥሬ ዕቃ የአቅርቦት ችግሮች፣ የ10 ዓመቱን ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የነዳጅ ድጎማና ሕገ-ወጥ ሽያጭ፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ተጀምረው የተጓተቱ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት መዘግየትን የተመለከቱ ጥያቄዎች የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በመዘጋጀት እየሰራች እንደምትገኝ አንስተው፤ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የ5 እና የ1 ዓመት የተግባር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም ከግብርና፣ ከኢንዳስትሪ እና ከአገልግሎት ዘርፉ ሀገሪቱ የ8.4 በመቶ ዕድገት ለማስመዝብ እየሰራች መሆኗን ገልጸው፤ ባለፉት 8 ወራት የተደገውን አበረታች ጥረት ማስቀጠል ከተቻለ ዕቅዱን ማሳካት እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡
በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ከወጪ ንግድ አንጻር ባለፉት ስምንት ወራት ኢትዮጵያ ያገኘችው ገቢ ከየትኛውም ዓመት የኤክስፖርት ገቢ እንደሚበልጥና በዚህም ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው ምርቶች 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ነው የተናገሩት።
በተያዘው በጀት ዓመት ለነዳጅ እና ለአፈር ማዳበሪያ 156 ቢሊየን ብር ድጎማ መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
ባለፉት 8 ወራት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ከ3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በቀጣይም ያለውን የስራ ፍላጎት በሚመጥን መልኩ ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መንግስት ጣልቃ በመግባት የኢኮኖሚ መሻሻያ ማድረጉንና በዚህም ተጨባጭ ውጤት ስለመገኘቱም አስረድተዋል፡፡
የሀይል አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በተከናወኑ ተግባራት በዘርፉ ኢነርጂ 100 በመቶ ተደራሽ ማድረግ መቻሉንና ከኢንዱስትሪ ግብዓት ጋር እንዲሁም መሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ መንግስት በርካታ ስራዎችን ስለማከናወኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives