"በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል" የተከበሩ ታገሰ ጫፎ
"በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል"
------ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ -----
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ጆ ሆ ያንግን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ጨምሮ የደቡብ ኮርያ ምክር ቤት ልዑካን ተገኝተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተከበሩ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሆኑ አገራት ቀዳሚ ናት ያሉ ሲሆን የደቡብ ኮሪያ መንግሥትና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ በሯ ክፍት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም የፋይናንስና የውጪ ምንዛሬ ሥርዓቷን ላይ ሪፎርም በማድረግ ለውጪ ኢንቨስትመንት ምቹ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አክለው ገልጸዋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በትምህርትና ሥልጠና፣ በህክምና እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች እያደረገ ላለው ድጋፍ አፈ ጉባኤው አመስግነዋል።
ደቡብ ኮሪያ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ትምህርትን በጥራት ለዜጎቿ ተደራሽ ለማድረግ የሄደችባቸው መንገዶች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን የተከበሩ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።
የደቡብ ኮሪያ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ጆ ሆ ያንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ባሳየችው አጋርነት የተነሳ በአፍሪካ ካሉ አገራት በተለየ ሁኔታ በደቡብ ኮሪያ መንግሥትና ህዝብ ዘንድ ቅድሚያ ይሰጣታል ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥትና ተቋማት በትምህርትና ሥልጠና በህክምና፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች በኢትዮጵያ እያከናወኑ ያሉትን ሥራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን ወጣቶችን የትምህርትና የሥራ ዕድል ፍላጎት ከግምት በማስገባት በኢትዮጵያ በሚገኙ ተቋማት የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናን ለደቡብ ኮሪያ ገበያ በስፋት ለማቅረብ ሰፊ የማስታወቂያ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ደቡብ ኮሪያ የገጠማትን የሰራተኛ እጥረት ለመቅረፍ የሌሎች አገር ዜጎችን ለመመልመል እያጤነች እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የሁለቱን አገራት የፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives