''ተለያይተን ሳይሆን ተደምረን ሀገራዊ ሠላምን ማረጋገጥ ይገባል'' 

-------- ምክትል አፈ ጉባዔ --------

(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 6 ፣ 2017 ዓ.ም፤ ተለያይተን ሳይሆን ተደምረን ሀገራዊ ሠላምን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ የኢፌደሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔና የፓርላማ ተመራጭ የሴቶች ኮከስ የበላይ ጠባቂ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ አስታውቀዋል።

የፓርላማ ተመራጭ የሴቶች ኮከስ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተካሄዷል።

የኮከስ የበላይ ጠባቂ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ እንዳሉት፤ ሴቶችን በማብቃት በሀገረ መንግስት ግንባታ ተሣትፏቸውን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

ሠላም የመጀመሪያም የመጨረሻ ጉዳያችን ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔ፤ የኮከሱ አባላት ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ  ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

መንግስት ከታጠቁ ኃይሎችና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ጠቁመው፤ ኮከሱ የምክር ቤቱን ተልዕኮ ሲፈጽም የሠላም ጉዳይን ሊያተኩርበት ይገባል ብለዋል።

እንደ ሀገር ያሉትን ችግሮች ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሀገራዊ ምክክር መድረክ በፌዴራል ደረጃ በሚደረገው  የአጀንዳ ልየታ ከሴቶችና ወጣቶች አንፃር የሚመለከታቸው እንዲሳተፉ ከወዲሁ ጥረት የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል።

ኮከሱ እስካሁን በውስጥና በውጪ አቅም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ትኩረት ያደረጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በመሠራቱ አባላቱ የማህበራዊና የመንግስታዊ ተልዕኳቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ  የወጡ ህጎችን በበጀት አስደግፎ ውጤታማ ሥራ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው፤ ዛሬ ላይ የኮከሱ አባላት ከአካባቢያዊ አስተሳሰብ  ወጣ ብለው እንደ ሀገር ማሰብ በመቻላቸው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላቸውን ገልፀዋል።

ሀገራዊ ሠላምን ለማረጋገጥ በሰለጠነና በዘመነ መልኩ መነጋገር የሚያስችል የምክክር ኮሚሽን፣ የሽግግር ፍትህና የተቋማት ሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮከሱ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።

የኮከሱ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ኪሚያ ጁንዲ በምክር ቤቱ የሴቶች ተሣትፎ  ከ41 በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀው፤ በቀጣይ በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከማን ጋር ምን መስራት አለብን የሚለውን በተደረጀ መልኩ በመለየት ውጤታማ ሥራ  እንደሚሰራ የኮከሱ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አለሚቱ አበበ ገልፀዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው በቀረበው የ3 አመት ተኩል የኮከሱ ዕቅድ  አፈፃፀም ሪፖርት  ላይ በኮከሱ አባላት ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።