ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፀደቀ

 (ዜና ፓርላማ) ሐምሌ 10 ቀን 2017 .ም፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2 አስቸኳይ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡

የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ ሪፖርት እና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፤ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም በፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዳደር፣ በምርጫ እና በምርጫ ስነ-ምግባር የባለድርሻ አካላት መብትና ግዴታ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጥርጣሬና ሥጋትን በማስወገድ ጊዜና ወጪን ሊቆጠብ በሚችል እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርና ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን  ሰብሳቢው አያይዘው አብራርተዋል፡፡

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት የታዩ እና ወደፊትም ሊከሰቱ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ሂደት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ወጣቶችን በምርጫ ለመሳተፍ እድል የሚፈጥር እና በምርጫ ሂደት የሚነሱ ቅሬታዎችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ አያይዘው አብራርተዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በምርጫ ጣቢያ የነበረው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ለምን ቀረ? በሚል ለቀረበ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፤ በየምርጫ ጣቢያዎች ኮሚቴ ከመዋቀሩ ይልቅ በክልል ደረጃ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለችግሩ በማዕከል ደረጃ ምላሽ እንዲሰጥበት ማድረግ እንደሚቻል የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ አስረድተዋል፡፡ 

የፓርቲ አባላት መዋጮ ክፍያን በተመለከተም 30 ወደ 20 በመቶ መቀነስ መቻሉን ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ይህ እንደግዴታ የማይታይ እንደሆነና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በራሳቸው ውስጠ ደንብና መመሪያ መሰረት መተግበር የሚችሉ መሆኑን የተከበሩ አቶ እውነቱ ጠቁመዋል፡፡

በሀገር ደረጃ አዳዲስ ክልሎች መመስረታቸው፤ ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት ከአሁን በፊት በአራት ክልሎች የድርጅት አባል ማፍራት አለባቸው የሚለው አሁን ላይ ወደ ስድስት ክልሎች እንዲያድግ መደረጉን የተከበሩ አቶ እውነቱ አለነ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ መሻሻሉ ለቀጣይ ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ የዲሞክራሲአዊ ስርዓትን ለመገንባት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው አንድ ጠንካራ ድርጅት መፍጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብትና የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር በግልፅ የተገኙ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በረቂቅ አዋጁ መመላከት እንዳለባቸው የተፎካካሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱ፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1394/2017 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡