አዋጁ ለወጣቶች ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
(ዜና ፓርላማ) ሐምሌ 10፣ 2017 ዓ.ም፤ የስታርታፕ አዋጅ ለወጣቶችና ታዳጊዎች ከፍተኛ የስራ እድል በመፍጠር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊና የቴክኖሎጂ እድገት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
ይህ የተገለጸው ምክር ቤቱ ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ሲሆን፣ የሃገርን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት እና ለወጣቱ ከፍተኛ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አዳዲስ የሀብት ምንጭ የሆኑ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን ለማበረታታት አዋጁ እንደሚያግዝ አባላቱ ተናግረዋል።
የስታርታፕ ፕሮግራም የተለያዩ የአስፈጻሚ ተቋማት፣ የፋይናንስ ድርጅቶችን እንዲሁም ባለሀብቶችን በማጣመርና በማስተሳሰር ምቹ የሆነ የኢኮኖሚ ስነ-ምህዳር መፍጠር የሚያስችል እንደሆነም አባላቱ ተናግረዋል፡፡
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የስታርታፕ ውጤት በሂደት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችንና ኩባንያዎችን በማፍራት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
ሰብሳቢው ስታርታፕ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል ።
አዋጁ ምቹ የስታርታፕ ምህዳርን በመገንባት ስታርታፖችን ውጤታማና ስኬታማ በማድረግ፤ ስታርታፖች እና የስታርታፕ ምህዳር ገንቢዎችን ዒላማ ያደረገ የተቀናጀ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል የተሳለጠ የስያሜ፣ የዕውቅና እና የአቅም ግንባታ አተገባበር ሥርዓት በመዘርጋት ቀጣይነት ያለው የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ እምርታን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።
ስታርታፖችን እና የስፓርታፕ ምህዳር ገንቢዎች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ተግዳሮቶች እና የፋይናንስ ስጋትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የግራንት ፕሮግራም፣ የብድር ዋስትና ማዕቀፍ እና የፈንዶች ፈንድ መዋቅር ማደራጀት የሚያስችል አዋጅ እንደሆነም ሰብሳቢው ገልጸዋል። ምክር ቤቱም አዋጁን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡