(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 19፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዳማ፤ ሴቶች በሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ልክ ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ በተከበሩ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ ተመላከተ።

ሰብሳቢዋ ይህንን ያመላከቱት፤ የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች እና እንክብካቤዎችን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ወቅት በሰጡት አስተያየት ነው።

ሰብሳቢዋ አክለውም፤ በምጣኔ-ሀብት ዘርፉ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ለሚገኙ ሴቶች በሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ልክ ክብር መስጠት እንደሚገባ፣ በመክፈቻ ንግግራቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት ዓሊ በበኩላቸው፤ ሴቶች በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ እና ምጣኔ-ሀብታዊ ዘርፉ በኩል ለውጥ እንዲያመጡ የተለያዩ የዓቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጣሉ ብለዋል።

ኃላፊዋ አያይዘውም የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች ሴቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርሱ ገልፀው፤ የኮከሱ አባላት በሚወጡ ሕጎች እና ፖሊሲዎች ረገድ እገዛ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሴቶች ማካተት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት የተቋማት ዓቅም ማጎልበት ባለሞያ አቶ እንየው ታምሩ በበኩላቸው፤ የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ ስራዎች መብዛት፣ የሴቶችን ጤና እንደሚጎዳ እና የመማር ዕድላቸውን እንደሚገድቡ አብራርተዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመፍታት፤ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ እንየው አክለው አስረድተዋል።

ስልጠናው በነገው ዕለትም ቀጥሎ እንደሚውል ከስልጠና መርኃ-ግብር መረዳት ተችሏል።

በ ፋንታዬ ጌታቸው