(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 6፣ 2015 ዓ.ም፤ በሴቶች እና ህፃናት ለይ የሚደርሰውን አስከፊ በደል እና ጫና ለመቀነስ የክልል ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አደረጃጀቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አደረጃጀት ዋና ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ኪሚያ ጁንዲ አስገንዝበዋል።

የተከበሩ ኪሚያ ይህንን ያሉት ጅማ በተካሄደው የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ የክልል ምክር ቤት አባላት እና የሴት ተመራጭ ኮከስ አደረጃጀት ሰብሳቢዎችን ባወያዩበት ወቅት ነው።

የሴቶች ኮከስ አደረጃጀቶች ከተወሰኑ ክልሎች በስተቀር በአዲስ መልክ መዋቀራቸውን የተረዱት የተከበሩ ወይዘሮ ኪሚያ፤ አሁንም አደረጃጀቱ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ወርዶ የሴቶችን ችግር ፈቺ ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሴቶች የምክር ቤት ተመራጭ ስንሆን የኢትዮጵያን ግማሽ ሕዝብ የወከልን መሆኑን ተገንዝበን ለሴቷ መብት መከበር እና እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ያሉት የተከበሩ ኪሚያ፤ የምክር ቤት ተመራጭ የኮከስ አባላትን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኮከስ አደረጃጀቶች ስኬተማ እንዲሆኑ የወንድ ተባባሪዎችን ማፍራት አስፈለጊ እንደሆነም ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ሰፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኮከሱ ስራ አስፈጻሚ አባል ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው በክልል ምክር ቤቶች የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች የሴቶችን ጥቅም ለማስከበር የኮከስ አደረጃጀቶች ተግተው ሊሰሩ እንደሚባ ተናግረዋል።

ሴትች በሁሉም ዘርፍ ብቁ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ሲሉም ወይዘሮ ወርቅሰሙ አክለዋል።

የክልል ምክር ቤት አባላት እና የሴት ተመራጭ የኮከስ አደረጃጀት ሰብሳቢ እና አባላት በበኩላቸው የኮከስ አደረጃጀቶች በሚገባ እንዲጠናከሩ በጀትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ