(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 4፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሻል አሳሰበ፡፡

ኮሚቴው ይህንን ያሳሰበው፤ ሰሞኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ክቡር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) የኮሚሽናቸውን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበው ባስገመገሙበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ኮሚሽኑ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከነበረበት 60 በመቶ ወደ 80 በመቶ አፈጻጸም መድረሱ፤ እንደዚሁም የፊስካል እና የበጀት አፈጻጸሙም ተመጣጣኝ መሆኑን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አፈጻጸሙ የተሻለ ነው የተባለው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እና ከዕቅዱ አንጻር እንጂ፤ ሀገሪቱ ከምትፈልገው የአገልግሎት አሰጣጥ እና ከዜጎች እርካታ አንጻር ከኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም፤ ኮሚሽኑ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚነሱ ቅሬታዎችን በ “ጊዜ የለኝም!” ዕሳቤ መፍታት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ በትኩረት አቅጣጫ ያስቀመጣቸውን ነጥቦች መተግበር እና ለውጡንም ከራሱ ከኮሚሽኑ፣ ከአመራሩ እና ከባለሙያው መጀመር እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የዘርፉ ለውጥም ሀገራዊ እንዲሆን ከፌዴራል እና ከክልሎች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም፤ ሲቪል ሰርቪሱ የተሻለ እና ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በማሰማራቱ ላይ ተግቶ እንዲሠራ እና ይህንን አቋሙንም በግልጽ ማሳወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ የኮሚሽኑ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም የተሻለ እንዲሆን ቋሚ ኮሚቴው በተጠናከረ ቼክሊስት ተደግፎ ተገቢውን ክትትል እንደሚያደርግ እና አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው በሚሄዱበት ጊዜ የተቻላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

የተከበሩ ሰብሳቢ፤ የኮሚሽኑን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ቀደም ብለው ለመገምገም መርኃ-ግብር ቢያዝም፣ በሥራዎች መደራረብ ምክኒያት መራዘሙን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ክቡር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጣቸውን ግብረ-መልስ ለቀጣይ ሥራዎቻቸው በግብዓትነት እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ