(ዜና ፓርላማ)፤ ነሐሴ 3፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ የሴቶች ኮከስ የሚያከናውናቸው ተግባራት፤ በሴቶች ሕይወት እና አኗኗር ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ እና የኮከሱ የበላይ ጠባቂ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ይህንን ያመላከቱት፤ በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ የኮከሱ የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ በተገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የሚደርስባቸውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ የምክር ቤቱ ኮከስ በቁርጠኝነት መሥራት አንዳለበትም፤ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ በዚህን ወቅት አስገንዝበዋል፡፡

በምክር ቤቱ ዐበይት ሥራዎች የሴቶች ኮከስ አባላት ተሳትፎ የላቀ እንዲሆን ተመራጭ ሴቶች በቅድሚያ ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸውም ምክትል አፈ-ጉባዔዋ አስታውሰዋል፡፡

የኮከሱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ኪሚያ ጁነዲ የኮከሱን የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሥራ አስፈጻሚው አባላት ባቀረቡበት ወቅት፤ በዝግጅት ምዕራፉ ኮከሱን መልሶ የማደራጀት፣ ኮሚቴ የማዋቀር እና የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ማዘጋጀት በጥንካሬ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተግባር ምዕራፍ ደግሞ ለኮከሱ አባላት እና የምክር ቤት አባላት ላልሆኑ ሴቶች ዘርፈ-ብዙ የዓቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውንም ወይዘሮ ኪሚያ አስረድተዋል።

በሰው-ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በተደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ፤ የምክር ቤቱ ኮከስም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከቱ በጠንካራ ጎን ከታዩ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአንጻሩ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች ፈንድ ከማፈላለግ እና የልምድ ልውውጥ ከማድረግ አኳያ፤ በኮከሱ አፈጻጸም በውስንነት የታዩ ጉዳዮች መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ኪሚያ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም የኮከሱ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በኮከሱ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አለሚቱ አበበ ቀርቦ ውይይት በተደረገበት ወቅት፤ ዕቅዱ በቀጣይ ትላልቅ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል እና እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ እንደሆነ በአስፈጻሚ አባላት አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡

የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት እንዳለባቸው እና በምክር ቤቱ የሚወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች ከሴቶች አኳያ የተቃኙ እንዲሆኑ ንቁ ተሳትፎ መደረግ እንዳለበትም በውይይቱ ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩልም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥረው የሚሠሩ እና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴቶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ስለሆኑ፤ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት በጋራ መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የኮከሱ የበላይ ጠባቂ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ የኮከሱ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስተካከያ እንዲደረግበት አሳስበው፤ በአንጻሩ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮች በየጊዜው ቅርጻቸውን እየቀያየሩ እየመጡ በመሆኑ፣ ወቅቱን የዋጀ አመራር ለመስጠት ራሳችንን ማብቃት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የኮከሱ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድም ውይይት ከተደረገበት በኋላ፤ በአስፈጻሚ አባላት መሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ቀን፡- ነሐሴ 3፣ 2014 ዓ.ም