«የሁለቱን ሀገራት የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር  በፓርላሜንታዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ይተኮራል»    የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)

(ዜና ፓርላማ) ፣ መጋቢት 15፣ 2013 ዓ.ም. ፤ አዲስ አበባ ፤ የኢትዮጵያን እና  ኔዘርላንድን የኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በፓርላሜንታዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ  ግንኙነት ላይ እንደሚተኮር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ሰብሳቢው ይህንን የገለጹት በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር  ሄንክ ጃን ባከርን  በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ  ከኔዘርላንድ ጋር ያላትን የኢንቨስትመንት ትስስር  ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ የሁለቱ ሀገራት ፓርላሜንታዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ  ግንኙነት አይተኬ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት የቆዬ ወዳጅነት እንዳላቸው የገለጹት ነገሪ (ዶ/ር) ፤ ወዳጅነቱ በኢንቨስትመንት  ፣  በትምህርት ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ  እንደሚጠናከር  ነው ለአምባሳደሩ የገለጹላቸው ፡፡

በተለይም የኔዘርላንድ ባለሃብቶች በኢትየጵያ  የአበባ ምርት ኢንዱስትሪ  ውስጥ  በስፋት እንደተሰማሩ  ነገሪ (ዶ/ር) ጠቅሰው ፣ ዘርፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት  ለባለሀብቶቹ ምቹ  ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ኢንቨስትመንቱን በሚፈለገው መጠን በተሟላ የሰው ሃይል ለማቀላጠፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ   የተመረቁ  ወጣቶች መኖራቸውንም ሰብሳቢው ጠቅሰዋል፡፡

ነገሪ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል የተወሰደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ለአምባሳደር ባከር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ግድቡ በዋናነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ያተኮረ እና   የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት 80 በመቶ የሚሆነው የገጠር ነዋሪ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ ያለመ ቢሆንም የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ግብጽ የተሳሳተ መረጃን ለአለም-አቀፉ ማሕበረሰብ በማሰራጨት ከነባራዊ እውነታው ውጭ መሆኗን ነው ለአምባሳደር ባከር የገለጹላቸው፡፡

መንግስት በትግራይ ክልል በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሰ መሆኑን  እና በዘመቻው የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየመረመረ አጥፊዎች ላይ ሕጋዊ  እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑን ሰብሳቢው    አክለው ተናግረዋል ፡፡

አምባሳደር ባከር በበኩላቸው ፤ ኔዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ የወዳጅነት ታሪክ  እንደላት ገልጸው ፣ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ከማስተሳሰር በተጨማሪም  የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ፣ በግብርናው ዘርፍ ፣ በትምህርት እና በስርዓተ-ጾታ  እንዲሁም   በመልካም አስተዳደር ዙሪያ  ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት  ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

የኔዘርላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሰማራታቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ፣ በተለይም ባለሃብቶቹ በአበባው ኢንዱስትሪ  ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ  ለኢንዱስትሪው ምቹ በመሆኗ ተመራጭ እንዳደረጓት ነው የተናገሩት ፡፡

ኢንቨስትመንቱ  በተፋጠነ መንገድ እንዲከናወን የኢንተርኔት ተደራሽነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት አምባሳደር ባከር ፣  ተደራሽነቱን  ለማስፋት  ኔዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል ፡፡

አምባሳደሩ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ከሁለት ሳምንት በፊት ተመልክተው መመለሳቸውን ገልጸው ፣ መንግስት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ አድንቀዋል ፡፡

ሀገራቸው አስፈላጊውን  የሰብዓዊ ድጋፉ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደር ባከር  አክለው  ጠቅሰዋል ፡፡

ዘጋቢ፤ ስሜነው ሲፋረድ