(ዜና ፓርላማ)፤ ጥቅምት 30፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በጥናት ላይ በማረጋገጥ፣ የሕግ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለይቶ በማሻሻል ወይም አዳዲስ ሕጎችን በማካተት ገቢ የመሠብሰብ አቅማቸውን አሟጥጠው መጠቀም እንደሚኖርባቸው ተብራርቷል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች በጋራ በተገኙበት በንብረት ላይ የሚጣለውን ግብር ማን መወሰን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር አድርገዋል።

መድረኩን በይፋ የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በንብረት ላይ ታክስ የመጣል ስልጣን ለፌዴራልም ሆነ ለክልል መንግሥታት በግልጽ ተለይቶ ያልተሰጠ መሆኑን አስታውሰው በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 99 ላይ ለፌዴራልም ሆነ ለክልል መንግሥታት በግልጽ ተለይቶ ያልተሰጠው ግብርና ታክስ የመጣል ስልጣን ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ እንደሆነ በግልጽ የተመላከተ በመሆኑ የዛሬው የምክክር መድረክ ዓላማም ምክር ቤቶቹ ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ለምክክር መድረኩ ዶ/ር ሲሳይ ረጋሳ በንብረት ላይ የሚጣለውን ግብር ማን መወሰን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ መነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የምክክር መድረኩን የመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ እቶ አገኘሁ ተሻገር ዜጎች የሚፈልጉትን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥና ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታቅዳቸውን እቅዶች ለማሳካት ለልማት እቅዶች ማስፈጸሚያ በግብርና በታክስ አማካኝነት የሚሰበሰበውን ገቢ በስፋት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ከዓመት ዓመት ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸውን እያሳደጉ ክልሎች ከፌዴራሉ መንግሥት ከሚያገኙት ድጎማ ተላቀው ወጪያቸውን በራሳቸው አቅም ከሚሸፍኑበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

አክለውም የተከበሩ አቶ አገኘሁ መንግሥት በሀገር ውስጥ ከሚፈጠረው ሀብት ተገቢውን ድርሻ ባለማግኘቱ ምክንያት በከተሞች እድገት፣ በወጣቶች የሥራ እድል ማግኘትና በአጠቃላይ በዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጠር እንደቆየ አስታውሰው መንግሥት እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ ከሚፈጠረው ሀብት በግብር እና በታክስ ገቢ ለመሰብሰብና የሰበሰበውን ገቢ ወደልማት ለማስገባት ጥረት እያደረገ ቢሆንም የዜጎችን ፍላጎት በበቂ ደረጃ ማሟላት ባለመቻሉ በዚህ ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ