(ዜና ፓርላማ)፤ ነሐሴ 10፣ 2014 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ በጎፋ ዞን ምርጫ ክልሎች የፌዴራል ፓርላማ ተወካዮች እና የክልል ምክርቤት አባላት ከመራጩ ሕብረተሰብ ጋር የውይይት መድረክ አካሄደዋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ መራጩን ሕዝብ በየጊዜው ማወያየት እና ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለማሰጠት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባ እንዲሄድ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ልማት እንዲፋጠን የማይተካ ሚና እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ የጎፋ ዞን ነዋሪዎች ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ ይህንን የገለጹት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና የክልል ምክር ቤት አባላት በጎፋ ዞን ምርጫ ክልሎች ከሕብረተሰቡ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በተካሄደው የመራጭ ተመራጭ ውይይት፤ ለረጅም ዘመናት ከሕብረተሰቡ ዘንድ ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በየደረጃው ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰጧቸውን ምላሾች በዝርዝር ተብራርተዋል።

በተመሳሳይም የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመቅረፍ፣ የልማት ስራዎችን ከማፋጠን እና የኑሮ ውድነትን ከመቆጣጠርና የገበያ ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር እርምጃዎች የተወሰዱ እንደሆነም በውይይቱ ተነስቷል።

እስከ አሁን የተከናወኑ አፈፃፀሞችን ያደነቁት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ በቀጣይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መፍታት ካለበት አበይት ጉዳዮች መካከል የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የኑሮ ውድነት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በውይይቱ ማጠቃለያ ባስተላለፉት መልዕክት የአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን በማጠናከር እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት መረባረብ የሚጠበቅብን ወቅት ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የተለመደውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባውም የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም እንደ ሀገር እየገጠመን ያለውን የኑሮ ውድነት ፈተና ለመቋቋም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በህዳሴ ግድባችን ላይ ባሳየነው ኢትዮጵያዊ አንድነትና ቁርጠኝነት ልንረባረብ ይገባል በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

አክለውም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በየደረጃው ለሚገኘው የመንግስት አስፈፃሚ አካል እንደሚያደርሱ እና አፈፃፀሙን እንደሚከታተሉም አፅዕኖት ሰጥተው ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡- የመንግስት ተጠሪ ፅ/ቤት
ቀን፡- ነሐሴ 10፣ 2014 ዓ.ም

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://youtu.be/kiCsgFwJzho 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ