(ዜና ፓርላማ)፣ ነሀሴ 11፣ 2015 ዓ.ም.፤አዲስ አበባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርዱ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችና የአሰራር ስርዓቱ ዙሪያ ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያየ፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8፣ 2015 ዓ.ም ባካሄደው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ያጸደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተልና እንዲመረምር በምክር ቤቱ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች፣ የአሰራር ስርዓትና የቀጣይ ዝርዝር ተግባራት ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች አቅርቦ ወይይት ተደርጐበታል፡፡

በውይይቱም ቦርዱ በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ለመመርመርና የመፍትሄ አካል ለመሆን የተሰጠውን ታሪካዊ አደራ የአገርና የሕዝብን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ ማከናወን እንዳለበትና ምክር ቤቱም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች አስታውቀዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርዱ በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት በየደረጃው ካለው የህብረተሰብ ክፍል ጋር እንደሚወያይና ውጤቱንም በህገ መንግስቱ በተቀመጠው አግባብ ለምክር ቤቱ በየወቅቱ ሪፖርት እንደሚያቀርብ እንዲሁም ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ተመላክቷል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ።