(ዜና ፓርላማ)፣ መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ መንግስት ከህወሃት ጋር የሀገሪቱን ጥቅም ያስከበረና ዘለቄታ ያለው ድርድር ለማድረግ ጥረት የሚያደርግ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዘዳንቷ ይህን የገለጹት ዛሬ በተካሄደው የሁለቱ ምክር ቤቶች ሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ነው፡፡

በዚሁም ወቅት መንግስት የሰላምና ዴሞክራሲ ጥያቄዎችን አንገብጋቢነት በመረዳት ከህወሃት ጋር የሀገሪቱን ጥቅም ያስከበረ ድርድር ለማድረግ መወሰኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን ይህንን የሰላም አማራጭ በመርገጥ ለሚደረግ ማንኛውም ትንኮሳ አስፈላጊውን የማስታገሻ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

እንደ ፕሬዘዳንቷ 2015 በጀት ዓመት ግጭቶች በውይይትና በድርድር የሚፈቱበት፣ የምክክር ኮሚሽኑ ተግባራት ተጠናክረው የሚሰሩበት፣ የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት፣ ሕዝቡ ካጋጠመው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማላቀቅ ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት ዓመት እንደሚሆንም ተብራርቷል፡፡

ፕሬዘዳንቷ አክለውም ሀገሪቱ ያጋጠማትን የዋጋ ንረት ለማረጋጋትና ጤናማ የማክሮ-ኢኮኖሚ ስርዓት እዲኖር ለማስቻል ውጤታማ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲ መተግበር ሌላው መንግስት በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚያደርግበት ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

በ ድረስ ገብሬ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ