(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 22፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ተቋማዊ አደረጃጀቱን እና ተጠሪ ተቋማቱን ለማቀናጀት ያከናወናቸውን የተቋም ግንባታ ተግባራት፤ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አደነቀ።

ቋሚ ኮሚቴው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና በተጠሪ ተቋማቱ የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሰሞኑን ባደረገው የመስክ ምልከታ ወቅት ነበር አድናቆቱን የገለጸው።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን የሰለጠነ እና ብቁ ክህሎት ያለውን የሰው ኃይል የማፍራት ኃላፊነቱን ለመወጣት፣ ተቋማዊ አደረጃጀቱን እና ተጠሪ ተቋማቱን ለማቀናጀት ያከናወናቸው የተቋም ግንባታ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን፤ በመስክ ምልከታው ወቅት መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

አገልግሎት ለመጀመር የተዘጋጀው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢሮ፤ ዕድሳቱ የተጠናቀቀው ነባሩ የቴክኒክ እና ሙያ ቢሮ ሲሆን፣ ከፍተኛ የኪራይ ወጪን እንደሚያስቀርም የኮሚቴው አባላት በምልከታቸው አረጋግጠዋል።

አባላቱ፤ የፌደራል ቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን እና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን የሥራ ሁኔታም ጎብኝተዋል። ከዚህም ባሻገር፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለይ የውጭ ሀገራት የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትን ለማርካት እንደዚሁም የሠራተኞችን ስምሪት እና የሥራ ላይ ደኅንነት ለመጠበቅ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሀገሪቱን የሚመጥን እጅግ የሰለጠነ እና ብቁ የሰው ኃይል በማምረት፣ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የሥራ ቅጥር ገበያዎች በማቅረብ፣ ሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በሚያረጋግጥ መልኩ ትርጉም ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

መሥሪያ ቤታቸውም በሥሩ ያሉትን ከ1 ሺህ 800 በላይ የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማትን እንደየአከባቢያቸው አንጻራዊ ዓቅም በማደራጀት፤ ምርታማ፣ ውጤታማ እና በክህሎት የበለጸገ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችላቸውን የስልጠና ሥርዓት ለመዘርጋት የሚረዳ ጥናት ተጠናቅቆ፤ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ሚኒስትሯ አያይዘው ተናግረዋል።