(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 10፣ 2014 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የ2012 በጀት አመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርትን መሠረት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው ዕለት ባደረገው ውይይት፤ ሚኒስቴሩ እስከ ሰኔ 10፣ 2014 ዓ.ም. ድረስ የኦዲት ግኝቱን ማስተካከያ እንዲያቀርብ በመንግስት ወጪ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተጠየቀ፡፡

በውይይቱም ስፖርት ሚኒስቴር፣ ባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የኦዲት ግኝቶች አስተካክሎ የእርምት ርምጃ በመውሰድ ረገድ በቋሚ ኮሚቴው ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ የሚከተሉት ለአብነት ይጠቀሳሉ። “ባልተሟላ ማስረጃ የተከፈለ ክፍያ፣ ያለ ውድድር የተፈጸመ ግዢ እና በመሥሪያ ቤቱ የስልክ ዝርዝር ውስጥ ላልተካተቱ ስልኮች የተከፈለ ብር 68 ሺህ 062 ብር ከ32 ሳንቲምን በሚመለከት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የማስተካከያ ርምጃ ለምን አልተወሰደም?”

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ቋሚ ኮሚቴው 21 የሚደርሱ ጥቄዎችን ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያቀረበ ቢሆንም፤ አጥጋቢ መልሶች እንዳልተሰጡት ግን አስረድቷል፡፡ ባልተሟላ ማስረጃ የተከፈሉ ክፍያዎችን ጨምሮ መመሪያ እና ደንብን ያልተከተሉ አሠራሮችን እንዲሁም ከስልጣኑ በላይ የመንግስት ሀብትን ለግሉ የተጠቀመ አካልን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ ገንዘብ ሚኒስቴር ለውስጥ ኦዲት ተገቢውን ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ አንስተው፣ መመሪያ እና ደንብን ባልተከተሉ አሠራሮች ላይ ተገቢው ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሰብሳቢው፤ የ2014 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እስኪጠናቀቅ ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በጋራ እየተንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ የኦዲት ግኝቱ በዋናነት ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴርን የሚመለከት ቢሆንም፣ ተወራራሽ በሆኑ እና የጋራ ተጠያቂነትን በሚያሰፍኑ የኦዲት ግኝቶች ዙሪያ የጋራ ዕቅድ አውጥተው እንዲሠሩ መክረዋል፡፡

አያይዘውም፤ የፋይናንስ ኃላፊዎች የሀገር እና የሕዝብ አደራ ያለባቸው በመሆኑ፤ ከኦዲት፣ ከሕጋዊነት፣ መመሪያን ተከትሎ ከመሥራት አንጻር ተጠያቂነት እንዳለባቸው ለሚመለከተው ሁሉ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር በዋናነት እንዲሁም ቱሪዝም ሚኒስቴር ሙሉ ትብብር በማድረግ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እስከ ሰኔ 10 ድረስ እንዲቀርብ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሰነድ አያያዙን እንዲያዘምን እና ለኦዲት ግኝት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ እንዲሁም ገንዘብ ሚኒስቴር ለሁሉም ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የስልክ ወጪ ጣሪያ አስቀምጦ አቅጣጫ እንዲያወርድ የሚሉት በቋሚ ኮሚቴው የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንደሆኑ አቶ ክርስቲያን አስገንዝበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ባልተሟላ ሰነድ የተከፈሉ ክፍያዎች ለትክክለኛው ዓላማ ውለዋል ማለት እንደማይቻል ገልጸው፣ የበጀት ዓመቱን ወጪዎች በሚመለከት በዕቅድ የተጠና በጀት ሊያቀርቡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሰነድ አያያዝ እና ምዝገባ የተቋሙ መሠረታዊ ችግር ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ያለአግባብ የተከፈሉ የስልክ ክፍዎች እንዲቋረጡ ርምጃ ባልወሰደው አካል ላይም ርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

በ ለምለም ብዙነህ