(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 01፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ ፕሮጄክቶች በተያዘላቸው መርኃ-ግብር እንዲጠናቀቁ ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደአለበት አሳሰበ፡፡

ኮሚቴው ይህንን ያሳሰበው፤ ሰሞኑን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተገኝቶ የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ነው ፡፡

ኮሚቴው በዚህ ወቅት፤ «በተለያዩ ቦታዎች ባደረግነው የመስክ ምልከታ፣ ለፕሮጄክቶች የተደረገው ክትትል እና ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን አረጋግጠናል» ብሏል፡፡

ፕሮጄክቶቹ በዘገዩ ቁጥር አላስፈላጊ ወጪ ስለሚጠይቁ በፍጥነት ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ሚኒስቴሩ ክትትል እና ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት፤ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር ኢንጂነር) አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ እና ከዓመታዊ የልማት ዕቅዳቸው የተመነዘሩ የመቶ ቀናት የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ፣ የዋጋ ግሽበት በምጣኔ-ሀብቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቆጣጠር የሚያስችል መርኃ-ግብር መነደፉን፣ ለከተማ ግብርና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑ፣ የዓመታዊ ሀገራዊ ምርት ግመታ ከአቅርቦት እና አጠቃቀም አንጻር ጊዜያቸውን ጠብቀው የተከለሱ መረጃዎች ለመንግስት እና መንግስታዊ ላልሆኑ ተጠቃሚዎች መሠራጨት መቻሉን፤ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ይገኙበታል ፡፡

ኮሚቴው በሌላ በኩል፤ የልማት ዕቅድ ዝግጅት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን፣ የአስፈጻሚ አካላት ሪፖርታቸውን በተቀመጡ የአፈጻጸም መለኪያዎች መሠረት ባለመላካቸው ተመሥርቶ የተወሰደ ተጠያቂነት አለመኖሩን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በሚገባ ማስተዋወቅ አለመቻሉን፣ የመረጃ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ የምርታማነትን ለውጥ በመስክ ግምገማ ጥናት በግብዓትነት ለመጠቀም ያላቸው አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ደግሞ በዕጥረት ጠቅሷል፡፡

በቀጣይ በዕቅድ የተያዙ ሀገራዊ ፕሮጄክቶች፤ በተያዘላቸው ጊዜ፣ ወጪ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ መሥሪያ ቤቱ የሚያደርገውን የክትትል፣ ድጋፍ እና ቁጥጥር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ሰብሳቢው በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በቀጣይ የዕቅዳቸው አካል በማድረግ እንደሚሠሩባቸው ገልጸዋል ፡፡

በመጨረሻም ኮሚቴው፤ በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ ተከላ አከናውኗል፡፡

በ ስሜነው ሲፋረድ