(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 10፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የ1ኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ ሁለት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ፡፡

ምክር ቤቱ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ የመራቸው ረቂቅ አዋጆች፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ባብራሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የኮርፖሬሽኑ ዋና ተግባር ሕብረተሰቡን ማሳወቅ፣ ማስተማር እና ማዝናናት በመሆኑ ተቋማዊ አሠራሩን ለማስተካከል ማሻሻያው እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታገሠ አክለውም፤ ኮርፖሬሽኑ ለአገራዊ አንድነት፣ ለብልፅግና እንዲሁም ለዴሞክራሲ ግንባታ ሕብረተሰቡን የሚያነሳሱ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂ አማካኝነት ሕብረተሰቡ የቴሌቪዥን ግብር የመክፈል ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 808/2006 የተቋሙን የገቢ ምንጭ በግልጽ ስለማያመላክት አዋጁ የነበረበትን ክፍተት ለመሙላት፣ የተቋሙን የፋይናንስ ዓቅም በመገንባት ተልዕኮውን በትክክል እንዲወጣ ለማድረግ እና ተጠያቂ የሚሆንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገም አብራርተዋል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ማሻሻያም ሲያብራሩ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ሀገራዊ እና ዓለም-አቀፍ ዜናዎችን እና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም-አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ለማሠራጨት ዋና የዜና ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም፤ ተቋሙ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ሀገራዊ ገጽታን ለመገንባት በአዋጅ ተልዕኮ ተሰጥቶታል ብለዋል።

በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የተካተቱት ዐበይት ጉዳዮች የተቋሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎችን አሿሿም፣ የእያንዳንዱን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ተጠሪነት እና የተቋሙን ሠራተኞች አስተዳደር በሚመለከት በግልጽ ለመደንገግ እንዲሁም ተቋሙ ገቢውን በነጻነት እንዲጠቀም ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ጋዜጠኛ ዐይኑ ያየውን፣ ጆሮው የሰማውን በትክክል በመዘገብ ለሕዝብ ማድረስ እንዳለበት ተናግረው፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንም ሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነጻ እና ገለልተኛ ተቋም መሆን እንዳለባቸው ተገናግረዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ አክለውም፤ እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ቁርሾን የሚያጠፉ፣ አንድነትን የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ከፖለቲካ ነፃ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም-አቀፍ መገናኛ ብዙኃናት የዜና ምንጭ መሆን እንዳለበት፤ የምክር ቤት አባላት ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ፤ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 9/2014 ሆኖ ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በሦስት ተቃውሞ፣ በሁለት ድምፀ-ተዓቅቦ ለዝርዝር ዕይታ በአብላጫ ድምፅ ተመርቷል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 10/2014 ሆኖ ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአምስት ድምፀ-ተዓቅቦ ለዝርዝር ዕይታ በአብላጫ ድምፅ ተመርቷል።

በ ጋሹ ይግዛው