(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 27፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2016 በጀት የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ማዕከል ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ በፌደራል መንግስት የ2016 ረቂቅ በጀት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር በዝርዝር ተወያይቷል፡፡

በውይይቱም የሚመደበው በጀት የተቋትን የማስፈጸም አቅም በሚያጎለብት እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲሁም የፋይናስ ደንብ እና መመሪያን ባከበረ አሰራር ተግባር ላይ ሊውል እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የ2016 በጀት የዜጎችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ፣ የዋጋ ግሽበትን እና ፍትሐዊ የልማት ጥያቄዎችን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ምክር ቤቱ አስገንዝቧል፡፡

የሀገሪቱ የ2016 በጀት የኢኮኖሚውን ዕድገት በተሻለ መልኩ የሚያፋጥን መሆን እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት ጠቁመው፤ በተለይም ገንዘብ ሚኒስቴር ለቴሌኮሙኒዩኬሽን፣ ለመንገድ ፕሮጀክቶች እና መብራት ኃይል የሚመደበውን በጀት በትክክል ተግባር ላይ ማዋል እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ለፕሮጀክት የሚመደበው በጀት ከብልሹ አሰራር የፀዳ እና የታለመለትን ዓለማ ለማሳካት መቻሉን ገንዘብ ሚኒስቴር መከታተል እንዳለበት አባላቱ አሳስበዋል፡፡

ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብአቶችን በማቅረብ አምራች ዘርፉ ዕራሱን በምግብ እንዲችል እና ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ ግብርናውን ወደ ዘመናዊነት ለማሻጋገር በፋይናንስ ዘርፉ መደገፍ እንደሚያስፈልግ የምክር ቤቱ አባላት ጠቁመዋል፡፡

ክልሎች ከፌደራል መንግስት የሚለቀቅላቸው የድጎማ በጀት በወቅቱ እየተሰጣቸው ባለመሆኑ የታቀዱ የልማት ስራዎቻቸውን በተገበው መንገድ ለማከናወን እየተቸገሩ በመሆኑ ገንዘብ ሚኒስቴር ለቀጣይ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ፤ ለልማት ተነሽዎች የካሳ ክፍያ፤ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ እያስነሱ በመሆኑ ገንዘብ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለችግሮቹ ዘላዊ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አመላክተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ፤ የሚመደበው በጀት የሀገሪቱን ማይክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ያደረገ እና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በ2016 በጀት መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር አቅዶ እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በጀትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ ለማዋል ትኩረት የተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራው የግል ሴክተሩን በማሳተፍ ከፍተኛ የሆነ የግል አምራች ባለሃብት ማህበረሰብ ለመፍጠር በፋይናንስ ዘርፉ መንግስት አስፈላጊውን ደጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት በሁለት በመቶ እንዳደገ ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በቀጣይ ክልሎች የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ እና ኢንቨስትመንትን በመሳብ የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚቻል አመላክተው፤ የተቋትማን የፋይናንስ የማስፈጸም አቅምን እና የሕግ ተገዥነትን ለማጎልበት የሚዲያ ሽፋን በመስጠት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የሀገር ውስጥ ወጭን የውስጥ የገቢ አቅምን በማሳደግ ለዕዳ ክፍያው ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡

በ መኩሪያ ፈንታ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ