ምክር ቤቱ ሁለት የሁለትዮሽ ስምምነቶችንና አንድ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ
(ዜና ፓርላማ)፤ መጋቢት 21፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት የሁለትዮሽ ስምምነቶችንና አንድ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ መንግስትና በስዊስ ኮንፌዴሬሽን መንግስታት መካከል እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሉግዘምበርግ መንግስታት መካከል የተደረጉ ናቸው።
የሁለቱን የሁለትዮሽ ስምምነቶች አስመልክቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ስምምነቶቹ ተደራራቢ ግብርን ለማስወገድና የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል፣ የአንዱ ሀገር ነዋሪዎች በሌላው ሀገር የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት የሠመረ እንዲሆን አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ ብለዋል።
ተጠሪ ሚኒስትሩ አክለውም፤ የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለሚደረገው የንግድ ልውውጥ፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንቅፋት እንዳይሆን ተደራራቢ ግብርን ማስቀረት ላይ ያለሙ ናቸው ብለዋል።
ምክር ቤቱም በስምምነቶቹ ዙሪያ ከተወያየ በኋላ በኢትዮጵያና በሉግዘምበርግ መካከል የተደረገውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 18/2015 እንዲሁም በኢትዮጵያና በስዊስ ኮንፌዴሬሽን መንግስታት መካከል የተደረገውን የሁለትዮሽ ስምምነት ደግሞ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 19/2015 አድርጎ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በተባባሪነት ደግሞ ለህግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል።
ምክር ቤቱ አያይዞም፤ የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
ማብራሪያውን ያቀረቡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የኢኮኖሚውን እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ እና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር የተሟላ ለማድረግ፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ለመገንባት እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምርምር ተቋማትና በኢንዱሰትሪ ትስስር ሂደት ለሚሰሩ ስራዎች ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ አክለውም፤ ረቂቁ በትስስር ለሚሰሩ ስራዎች ምቹ ሁኔታንና አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሳለጥ፤ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ምክር ቤቱም ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ፤ ከምክር ቤት አባላት የተሰነዘሩ አስተያየቶችን በማካተት ረቂቁን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 17/2015 አድርጎ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በተባባሪነት ደግሞ ለኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል ።
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives