(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 1፣ 2014 ዓ.ም.፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 16ኛ መደበኛ የመዝጊያ ጉባዔው ሁለት ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 804/2005 ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን በዋናነት ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መምራቱን አስታውሰው፤ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የተዘጋጀው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ ዕድል ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሰረት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ከምክርቤቱ የህግ ባለሙያዎች ጋር በጋራ ረቂቅ አዋጁን በጥልቀት መመርመራቸውን እና አዋጁን ካዘጋጁ አካላት እንዲሁም የህዝብ ውይይት መድረክ በማዘጋጀት አዋጁን ለማሻሻል ግብአት የሚሆኑ በርካታ አስተያየቶች መሰብሰባቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከቃላትና ሀረጋት ብያኔ ጀምሮ በርካታ የአዋጁ አንቀጾች መሻሻላቸውንና አዳዲስ ሀሳቦች መካተታቸውን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውና ተጨማሪ ስልጣንና ተግባር እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የወጣውን ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1276/2014 ዓ.ም አድርጎ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜናም ምክር ቤቱ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት (አካፓድ) የተቋቋመበት የተሻሻለውን የጆርጅታውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በተከበሩ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

የስምምነት ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ከተካተቱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት እና ከጎኗ እንዲቆሙ ለማድረግ የሚያስችል እና ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ሰብሳቢ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት (አካፓድ) የተቋቋመበት የተሻሻለው የጆርጅታውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1277/2014 ዓ.ም. ሆኖ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ