(ዜና ፓርላማ)፣ ሐምሌ 21፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ምስጋና አቅርቧል፡፡

“አንድ ሆነን እንስራ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፍ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የምስጋና መርሃ ግብር የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፤ ሁሉም ቀኝ እጃቸውን ግራ ደረታቸው ላይ በማድረግ ለአንድ ደቂቃ ከቆሙ በኋላ፣ በጭብጨባ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከፍ ያደረጉትን ጀግኖች አትሌቶችን አመስግነዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ባስተላለፉት መልዕክት በወሳኝ ሰዓት የኢትዮጵያን አንድነት ያስመሰከሩትን አትሌቶች እና የቡድኑን አመራሮች በሙሉ አመስግነዋል፡፡

የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባዔ አክለው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ውድቀቷን ሲጠባበቁ ባሉበት በዚህ ወቅት ሀገራችን በጀግኖች ልጆቿ ደማቅ ድል ተጎናጽፋ በዓለም አደባባይ ዳግም ደምቃና አሸብርቃ ሰንብታለች ብለዋል፡፡

“እኛም የነሱን ፈለግ በመከተል በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ተግተን ልንሰራና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጠነከረ መንፈስና በአሸናፊነት ስሜት ልዩነቶቻችንን አጥብበን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ ተናበንና ተግባብተን የሀገራችንንና የህዝባችንን ብልጽግና እውን ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እናድርግ“ በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በ አበባው ዮሴፍ