(ዜና ፓርላማ)፤ መጋቢት 26፣ 2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው13ኛው መደበኛ ጉባዔው የአንድ የምክር ቤት አባልን ያለመከሰስ መብትን አንስቷል።

የውሳኔ ሀሳቡ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ ቀርቧል።

ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ጥያቄ የቀረባቸው የተከበሩ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ሲሆኑ፤ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ከመንግስት የግዥ አሰራር ውጪ የተጋነነ ግዥ እንዲፈፀም በማድረግ፣ በስማቸው በተመዘገበ የባንክ አካውንት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በመግባቱ፣ በባለቤታቸው ስም የመኖሪያ ህንጻ ተመዝግቦ በመገኘቱ በዋነኛነት ተጠርጣሪ የሆኑባቸው ነጥቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የተከበሩ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቀረበውን ያለመከሰስ መብት ተከላክለዋል።

በምክር ቤት አባላት በኩል ያለመከሰስ መብቱ እንዲነሳ ከመቅረቡ በፊት አባሉን ማነጋገራቸውን እና ተገቢው የማጣራት ስራ መሰራቱ ተገልጿል።

ምክር ቤቱም በተከበሩ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) በቀረበው ያለመከሰስ መብት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ያለመከሰስ መብታቸውን በውሳኔ ቁጥር 16/2015 ዓ.ም በ 1 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አንስቷል።

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ