(ዜና ፓርላማ)፣ ሰኔ 15፣ 2015 ዓ.ም፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ጉባዔው የቀረቡለትን ሁለት ረቂቅ ደንቦች መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡

ረቂቅ ደንቦቹ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ክፍያን ለመወሰን የቀረበ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ናቸው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ረቂቅ ደንቦቹን አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ቀደም ሲል የነበረው ደንብ ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያስከፍሉ የሚያደርግ ቢሆንም ለሰባ ዓመታት ያገለገለ በመሆኑ ይህም ወቅቱን ያገናዘበና የስራውን ውስብስብነት ከግምት ያስገባ መሆን ስላለበት ደንቡን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም ጥያቄና አስተያየት የሰጡ ሲሆን በተለይ የክፍያ ሁኔታ ከፍ ካለ የከሳሾች ቁጥር እንዲቀንስና ክሳቸውን ወደ ፍርድ ቤት እንዳያመጡ በማድረግ የፍትህ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በቋሚ ኮሚቴው በኩል ቢታይ በማለት አስገንዝበው፤ መክፈል የማይችሉትን ዜጎችም ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ 

ረቂቅ ደንቡም ደንብ ቁጥር 26/2015 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብን በዝርዝር ከመረመረ በኋላ ትኩረት ተሰጥቶ ሊታዩ ይገባል ያላቸውን ነጥቦች በማካተት ረቂቅ ደንብ ቁጥር 27/2015 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በ እያሱ ማቴዎስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡- 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR 
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ