ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ

 (ዜና ፓርላማ) ሰኔ 24 ቀን፣ 2017 .ም፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 41 መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የውሳኔ ሀሳብ በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (/) አቅርበዋል፡፡

የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በተመለከተ ቀደም ሲል ሲሠራባቸው የነበሩት አዋጆች ክፍተቶች የነበሩባቸው በመሆኑና በጊዜ ሂደት አዋጆቹ ያላካተቷቸውን ጉዳዮችን በመለየት ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አዋጅ እንደሆነ ነው በውሳኔ ሀሳቡ የተነሳው፡፡

የቀድሞቹ አዋጆች የቤት ውስጥ ሠራተኛ፣ የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ ውጭ የትምህርት ዝግጅት የማይጠይቁ የሥራ ዓይነቶችን ባለማካተታቸው ክፍተቶች የተፈጠሩ ስለመሆኑም የተከበሩ ነገሪ (/) ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ አመላክተዋል፡፡

አዋጁ ሕገ- ወጥ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለመከላከልና በውጪ ሀገር ሥራ ስምሪት የዘመነ የአንድ ማዕከል የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

በውጪ ሀገራት ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል ላኪ ኤጀንሲዎች ተመጣጣኝ የዋስትና ገንዘብ እንዲያስቀምጡ በማድረግ የዜጎች እንግልት የሚያስቀር አዋጅ ስለመሆኑም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተብራርቷል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል ረቂቅ አዋጁ ዜጎች በሰለጠኑበት ሙያ ብቃታቸውን በቴክኖሎጂ በማረጋገጥና ከዚህ ቀደም የነበሩ ተግዳሮቶችን በማስቀረት እንደ ሀገር ተወዳዳሪ እንድንሆን የሚያስችል ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

በሀገራችን በተለያዩ የሙያ መስኮች የካበተ ልምድ ኖሯቸው መደበኛ ትምህርት ያልተከታተሉ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ የብቃት ምዘና ስርዓትንም መከተል እንደሚገባ በአዋጁ ስለመደንገጉም ሚንስትሯ አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ዜጎችን ከህገ ወጥ ደላሎች የሚታደግና ህገ ወጥ የዜጎች ዝውውርን በማስቀረት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1389/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡