ምክር ቤቱ የውሃ አካል ዳርቻ አወሳሰን፣ ልማት  እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ

 (ዜና ፓርላማ) ግንቦት 14 2017 .ም፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 31 መደበኛ ስብሰባው፤ የውሃ አካል ዳርቻ አወሳሰን፣ ልማት  እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ደምጽ አጽድቋል፡፡

የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አወቀ አምዛዬ (/ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የውሃ አካል ዳርቻን በዘላቂነት ለማልማትና መንከባከብ የውሃ ስነ-ምህዳር አግልግሎትን በማሻሻል  ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ መሆኑን የተከበሩ አወቀ አምዛዬ (/አስረድተዋል፡፡

የውሃ አካል ወንዝ ዳርቻን፣ ሐይቅ፣ ግድብ፣ ውሃ አዘል መሬት፣ ምንጭ  እና የከርሰ ምድር ውሃ አያያዝ እና አጠቃቀምን  የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አወቀ (/አመላክተዋል፡፡

በተከለለ የውሃ አካል ዳርቻ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነባር ልማት ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል የሚችለው በውሃ አካሉና ብዝሃ ህይወቱ ላይ ጉዳት እና ብክለት የማያስከትል መሆኑ አግባብ ባለው አካል ሲረጋገጥ መሆኑን የተከበሩ አወቀ አምዛዬ( / ) አስገንዝበዋል፡፡

የውሃ አካል ዳርቻ ልማትና እንክብካቤ የአካባቢ ማህበረሰብን በሚያሳትፍ እና ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ አግባብ ባለው አካል ታቅዶ እንዲተገበር ይደረጋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ሀገራዊ አረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማፋጠን እና የወንዝ ዳር አትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡

የውሃ አካል ዳርቻን ማልማት በአዋጅ መደንገጉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ወንዞች በደለል እንዳይሸፈኑ ለመከላከል እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡

የወንዝ ዳርቻዎችን ለማልማት ረቂቅ አዋጁ ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ጠቁመው፤ የአፈፃፀም መመሪያ  በማውጣት  ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው ፍሳሽ ለወንዝ ዳርቻው የብክለት መንስኤ እየሆነ የመጣ በመሆኑ ይህን ለመከላከል እና ለመቆጣጣር በአዋጁ መመላከት እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ የውሃ አካል ዳርቻ አወሳሰን፣ ልማት እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1382/2017 አድረጎ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡