ምክር ቤቱ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፀደቀ
ምክር ቤቱ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፀደቀ
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 41ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦችን የሚያሳልጥ እና የሀገሪቱን የውጭ ዲፕሎማሲ ለማሻሻል የበኩልን ሚና የሚጫወት መሆኑን የተከበሩ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ አያይዘው አስረድተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት የህግ ማዕቀፍ መሆኑን የተከበሩ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን ዶ/ር መሬት የመንግስት እና የህዝብ ሀብት በመሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ፈቃድ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ እንጂ በሪልእስቴት ዘርፉ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ አዋጅ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅርፍ፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥ ሚናው የጎላ እንደሚሆን የተከበሩ እሸቱ ተመስገን ዶ/ር ጠቁመዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አዋጁ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን እንዳያጣብብ እና የኑውሮ ውድነትን እንዳያባብሰው ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አያይዘውም የውጭ ሀገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት በአንድ ዋና ከተማ ብቻ እንዳይወሰን እና የመሬት ጥበት እንዳይከሰት በሁሉም አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ዙሪያ፤ የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ከሚመለከታቸው አካላት በቂ ውይይት ማድረጋቸውን ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ፤ የውጭ ሀገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1388/2017 አድርጎ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives