(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 8፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገነዘቡ፡፡

ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት፤ በምክር ቤቱ የሴት ተመራጮች ኮከስ አስተባባሪነት እና በጤና ሚኒስቴር ዐቢይ ባለድርሻነት፣ "የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ትግበራን ቀጣይነት ማረጋገጥ" በሚል ርዕስ፤ ለምክር ቤቱ አባላት እና ለሴክተር መሥሪያ ቤቶች አመራር አካላት በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡

በንግግራቸውም፤ በየዓመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት በፊት ከነበረው በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም፣ አሁንም ከመቶ ሺህ እናቶች ውስጥ 4 መቶ 01 እናቶች በወሊድ እና በተያያዙ ችግሮች እንደሚሞቱ መረጃዎች ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡

ይህንን የእናቶች ሞት ጉዳት ለመቀነስ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ ቀዳሚው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመው፤ እናቶችን ከሞት ለመታደግ አገልግሎቱን በሁሉም ቦታ እና ለሁሉም ዜጋ በተጠናከረ መልኩ ማዳረስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም አሁን ላይ ሀገሪቱ በገጠማት ፈተና በርካታ የጤና ተቋማት በመውደማቸው እና በመዘረፋቸው ምክኒያት የጤና ዘርፉ ክፉኛ በመጎዳቱ፤ ዜጎች ለከፍተኛ የጤና ችግር፣ ስቃይ እና ሞት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን የጤና፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እና ግብዓቶች ማግኘት እንዲችሉ፤ መንግስት ከሚሠራው ጎን ለጎን ውሳኔ ሰጪ አካላት በተለይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ የጤና ሚኒስቴር መድረኩን በማመቻቸቱ አመስግነው፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት በአግባቡ አለመተግበር ለእናቶች ሞት መንስዔ ከመሆኑም ባሻገር፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ጭምር የሚጎዳ በመሆኑ ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ምክር ቤቱም ሆነ የምክር ቤቱ አባላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት፤ ለስኬታማነቱ እንደሚጥሩም አስታውቀዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የፕሮግራም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በወሊድ ዕቅድ አገልግሎት ረገድ በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም በሀገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የወሊድ መጠን መኖሩን እና ይህም በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የሚሆኑ ግብዓቶች ከሌሎች ሀገራት በድጋፍ የሚገኙ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከሀገራቱ የሚደረገው ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን አስታውሰዋል። እንዲሁም አልፎ አልፎ ሕብረተሰቡ የቤተሰብ ዕቅድን ከተለያዩ አስተሳሰቦች ጋር በማገናኘት፤ በአግባቡ ያለመተግበር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን በተግዳሮትነት አንስተዋል፡፡

ስለሆነም ለሥራው ማስፈጸሚያ የሚሆን የበጀት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እና ይህንን የተሳሳተ አመለካከት በማረሙ ረገድ የምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ፤ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በሕብረተሰቡ አመለካከት ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት እና ከተሳታፊ አካላት በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የምክር ቤት አባላት በተጨማሪም አጀንዳው በዚህ ወቅት መቅረቡ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ ወደ መራጩ ሕዝብ የሚሄዱ በመሆናቸው፣ ከሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በማቀናጀት በትኩረት እንደሚወያዩበት አመላክተዋል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ