(ዜና ፓርላማ)፣ መጋቢት 19፣ 2015 ዓ.ም፤ ሰላም ከጦርነት ያልተናነሰ ትጋት ስለሚጠይቅ ዘላቂ ሠላም ማስፈን ይቻል ዘንድ እያንዳንዱ ህብረተሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሳስበዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎችን አንስተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽ ተሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት አሁን ላይ ሰላምን በተመለከተ ከዛሬ ስድስት ወር የተሻለ ሁኔታ እንዳለ ገልጸው፤ ወደ ተሟላ ሰላም ለመሄድ ግን በርካታ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሰላም ከጦርነት ያልተናነሰ ጀግንነትና ትጋት ስለሚጠይቅ በአንፃራዊነት የተገኘውን ሠላም ለማስቀጠል የምክር ቤቱ አባላትና ህብረተሰቡ የጐላ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ፖለቲካ የመተላለፍ፣ የሴራ እና የጉልበት ፖለቲካ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት አልፏል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ነገር ግን ጦርነት እንደቆመ ወዲያውኑ ሰላም እንደማይሰፍንና የድኅረ ጦርነት አውድ ጫና ስለመኖሩ ጠቁመዋል።

የጦርነት ነጋሪትን አብዝተው የሚጎስሙ፣ ጦርነትን የሚሰብኩ፣ ግጭት የሚፈበርኩና አዛብተው የሚዘግቡ ኃይሎች በመኖራቸው የሰላም አየር ለማስፈን ፈተና ቢሆንም፤ ሰላም ለማስፈን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተሟል ሰላም ይኖር ዘንድ መንግስት ኦነግ ሸኔን ጨምሮ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ እና ቅማንት አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ እንደሆነም ዐቢይ (ዶ/ር) አንስተዋል።

በ አበባው ዮሴፍ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ