(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 22፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ስታቲስትክስ አገልግሎት የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነቱን እንዲያሻሽል አሳሰበ፡፡

ኮሚቴው ይህንን ያሳሳበው፤ የኢትዮጵያ ስታቲስትክስ አገልግሎትን የ2012 የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ይፋዊ የሕዝብ የውይይት መድረክ ነው፡፡

ሀገራችን ካላት ውስን ሀብት ተቆርሶ ለተቋሙ የተበጀተው የገንዘብ መጠን በሥራ ላይ ሊውል ሲገባው፤ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ አለመሆኑ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉድለቶች ላሉባት ሀገር የሚመጥን አለመሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በፕሮግራም ከተደለደለለት መደበኛ በጀት፤ ከ178 ሚሊዮን ብር በላይ በሥራ ላይ አለማዋሉን፤ ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ግኝቱን ጠቅሶ አስረድቷል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ በአገልግሎቱ የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ያመላከተው ቋሚ ኮሚቴው፤ ነገር ግን ይህንን በጀት አገልግሎቱ ካልተጠቀመው በወቅቱ አሠራርን ተከትሎ ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ ማድረግ እንደነበረበት አስታውሷል፡፡ በቀጣይ በአጭር ጊዜ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የተገኙት ግኝቶችም አብዛኛዎቹ የአሠራር ክፍተቶች በመሆናቸው፤ እነዚህን ክፍተቶች በፈጠሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው ባስቀመጠው አቅጣጫ አመላክቷል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ፤ በተቋሙ የኦዲት ግኝቱን በሚመለከት የታዩ ለውጦች ቢኖሩም፣ ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ መቅረብ የሚገባው ሰነድ ቀርቦ፤ መወራረድ ያለበትን በማወራረድ፣ ወደ መንግስት ካዝና መመለስ ያለበት ሊመለስ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስትክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በበኩላቸው፤ በየጊዜው ክትትል እና ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ በገንዘብ ሚኒስቴር የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዓት መሠረት ለመሥራት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን እና ከሐምሌ ወር ጀምሮ በሁሉም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው፤ የኢትዮጵያ ስታቲስትክስ አገልግሎት የተገኘበትን የኦዲት ግኝት አስመልክቶ የወሰዳቸው የእርምት ርምጃዎች እንዳሉ ሆነው፣ በቀጣይ በድጋሚ መሻሻል ይገባቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

አገልግሎቱ፤ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መርኃ-ግብሩን እስከ ሐምሌ 5፣ 2014 ዓ.ም. እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዓት መሠረት እንዲሠራ በተጨማሪም የኦዲት ግኝቶችን የዓመታዊ ዕቅዱ አካል በማድረግ እንዲንቀሳቀስ እና ተሰብሳቢ ሒሳብን በአጭር ጊዜ ማስመለስ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተከትሎ እንዲያስመልስ ተነግሮታል፡፡

በሌላ በኩል የገንዘብ ሚኒስቴር ከገንዘብ አስተዳደር ጋር ተያይዞ ጥብቅ ቁጥጥር አድርጎ ርምጃዎችን በመውሰድ፤ በ2 ወራት ውስጥ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚሉ እና በተለይም የበጀት አጠቃቀም ውጤታማነቱን በተመለከተ ቀጣዩ ዕቅድ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሊሆን እንደሚገባው፣ ቋሚ ኮሚቴው ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ጠቁሟል፡፡

በ ለምለም ብዙነህ