በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ-ልማት እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሻሸመኔ ከተማ ከደረሰባት አለመረጋጋት እና አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥታ በልማት እንቅስቃሴ መገኘቷን አደነቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በሻሸመኔ ከተማ ባደረገው የመስክ ምልከታ፤ የከተማውን ስም፣ ልማት እና መልካም ገጽታ የሚጎዱ ተወጋዥ ተግባራት የፈጠሩትን አሻራ ታዝቧል፡፡ ይሁን እንጂ አስከፊውን ሁኔታ ለመቀልበስ በተሠራው የልማት፣ የሰላም እና የገጽታ ግንባታ ክንዋኔዎች፤ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ መንግስት፣ በፌዴራል ድጋፍ እና በከተሞች ተቋማዊ እና የመሠረተ-ልማት ማጎልበት መርኃ-ግብር (UIIDP) የሚሠሩ ፕሮጄክቶች ወቅታዊ አፈጻጸም፤ የከተማው አመራር የቅርብ ክትትል እና ቁጥጥር አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማሳያ መሆናቸውንም ገምግሟል፡፡ የመሠረተ-ልማት ሥራዎችም፤ የከተማውን ሕብረተሰብ ጥያቄ እና ፍላጎት አማክለው እንዲቀጥሉ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ የተከበሩ ፍራኦል ኡዴሳ፤ የሻሸመኔ ከተማን የልማት እና የብልጽግና ማዕከል እንዲሁም ምቹ እና ሳቢ በማድረግ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው እንድቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ በከተማ ግብርናው ዘርፍ ደግሞ፤ ያሉትን ባዶ ቦታዎች ለይቶ ማልማት፣ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የከተማው ከንቲባ ክቡር ወሾ ከድር በበኩላቸው፤ የከተማውን የውኃ ችግር ቀርፈው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን፤ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም፤ በከተማው በጀት ከሚሠሩት 38 ፕሮጄክቶች መካከል 28ቱ የተጠናቀቁ ሲሆን፣ 8ቱ በመጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም አምስቱ ከባለፈው በጀት ዓመት የተሻገሩ ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ በከተማው ባሉ ድርጅቶች እና የሕብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ያሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን 84 ፕሮጄክቶች፤ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተገኘው በጀት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴ አብራርተዋል፡፡

ከተማው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ሕዝባዊ የሸንጎ ሥርዓት መጠቀሙ መልካም ሆኖ፤ ተመሳሳይ ሥርዓት በቀበሌዎችም ቢተገበር የሚበረታታ እንደሆነ አመልክቷል-ቋሚ ኮሚቴው፡፡

በሌላ በኩልም የሻሸመኔ ከተማን የቆሻሻ ማስወገጃ ችግር ለቀጣይ ሁለት አስርት ዓመታት ሊፈታላችው የሚችል ፕሮጄክት ተጀምሮ፣ ቁፋሮው ተጠናቆ፣ ግንባታው ብቻ መቅረቱን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ገምግሟል፡፡

የፌዴራል የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጄክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ በበኩላቸው፤ ሴፍቲኔት፣ ዓቅመ-ደካሞችን ለማበረታታት እና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የተጀመረ ልማታዊ ፕሮጄክት መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

እንደዚሁም ከመሬት አያያዝ እና አስተዳደር ረገድ ይዞታዎችን ለይቶ ከመያዝ፣ ከማስተዳደር እና ወደ በይነ-መረብ ከመቀየር አኳያ የሚስተዋሉት ጅምር ሥራዎች፤ በቀጣይ በቂ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊጠናቀቁ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡