(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 17፣ 2014 ዓ.ም.፤ ሰንዳፋ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ሰንዳፋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ድንገተኛ ምልከታ አካሄደ።

ሰሞኑን በተካሄደው በዚህ ምልከታ፤ ዩኒቨርስቲው እያከናወናቸው ያሉ ጠቅላላ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴዎች፣ የሪፎርም ተግባራቱ፣ የወንጀል መከላከል፣ የአስተዳደር እና የማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት፣ የጥናት እና ምርምር አንዲሁም በስነ-ምግባር የታነፀ ፖሊስ ከመፍጠር አኳያ ያለበትን ደረጃ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ጋር ተወያይቷል፤ በመስክ ምልከታም አዳብሮታል።

በዩኒቨርስቲው የሚማሩ ተማሪዎችን ጊዜው ከሚጠይቀው ሳይንሳዊ ጥበብ እና የረቀቀ ቴክኖሎጂ ጋር አሰናስሎ በሥራ ከማሰማራት አኳያ ዩኒቨርስቲው የሄደበት ርቀት አስደሳች መሆኑን፤ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

ዩኒቨርስቲውን በአፍሪካ ተመራጭ የፖሊስ ዩኒቨርስቲ ከማድረግ አኳያ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ለማጎልበት፣ ዲጅታል የመረጃ አያያዝን ለማስፋት፣ ሴት የፖሊስ አመራሮችን ለማፍራት እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፤ ዩኒቨርሲቲው ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በተደረገው የሕግ ማስከበር ሂደት ከመከላከያ ቀጥሎ የፖሊስ አባላት የከፈሉት መሥዕዋትነት ከፍተኛ እንደነበረ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስታውሰዋል። በአንጻሩም ወንጀልን አስቀድሞ ከመከላከል እና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ፈጥኖ ወንጀሎኞችን ወደ ሕግ ማምጣት የሚችል ዘመኑን የዋጀ የፖሊስ ሠራዊት በመገንባት ሂደት፤ የዩኒቨርስቲው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ የተከበሩ መስፍን እርከቤ አስገንዘበዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ፤ ዩኒቨርስቲው በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ የፖሊስ ሳይንስ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ መርኃ-ግብሮችን በዲፕሎማ፣ በዲግሪ እንዲሁም በድኅረ-ምረቃ ደረጃዎች በመክፈት ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲው በዋናነት ጥራት ያለውን የፖሊስ ትምህርት እና ስልጠና መስጠት፣ ዘመን-አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም፣ እንዲሁም ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የትምህርት ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ዩኒቨርሲቲውን በአፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ጨምረው አብራርተዋል።

በ ሚፍታህ ኪያር