ቋሚ ኮሚቴው በፌደራል ፍርድ ቤቶች  የ2014/2015 ዓ.ም. የፕሮግራም በጀት ላይ ተወያየ  

(ዜና ፓርላማ) ፣ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ፤ አዲስ አበባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን የ2014/2015 ዓ.ም የፕሮግራም በጀት አስመልክቶ  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ  አካላት ጋር ተወያይቷል ፡፡

የፕሮግራም በጀቱን   የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ  በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ፣ በጀቱ  የመሰረተ ልማት እና  ተቋማትን በዘመናዊ  ቴክኖሎጂ በማዘመን ቀልጣፋ የሆነ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ፕሬዝዳንቷ ይህንን ይበሉ እንጂ የቋሚ ኮሚቴው አባላት  የቀረበው  የፕሮግራም በጀት  በአብዛኛው የገንዘብ ሚኒስቴር ያስቀመጠውን የበጀት ጣሪያ  የተላለፈ በመሆኑ  የሀገሪቷን የገቢ አቅምና ወጪ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ መቅረብ እንዳለበት አስተያየታቸውን ገልጸዋል ፡፡

 የፍርድ ቤቶችን ስራ ለማቀላጠፍና የዜጎችን የፍትህ እርካታ ታሳቢ ያደረገ  በጀት ምክንያታዊ  በሆነ መንገድ ቀርቦ በልዩነት መታየት እንዳለበት ከሕግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ   አስተያየት ተሰጥቶበታል ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ  አቶ ተፈሪ ደመቀ በበኩላቸው  ፕሮግራም በጀቱ የሀገሪቷን አቅም  ባገናዘበና ዕቅድና በጀትን አስተሳስሮ መቅረብ  እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነይ በበኩላቸው ውይይቱ ምክንያታዊ  የሆነ በጀት መቅረቡን ለማረጋገጥ  ያለመ መሆኑን አስረድተው ፣ የቀረበውን  የ2014/15 የፕሮግራም በጀት ሃሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡም  ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በተሰጠው አስተያየት መሰረት  የፕሮግራም በጀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተገቢው መረጃ ተብራርቶ  እንደሚቀርብ  ተናግረዋል፡፡

በፋንታዬ ጌታቸው