(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 8፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት እና ትራስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ተውጣጥተው ከመጡ ምሁራን ጋር፣ የ 'ማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ናቸው' ብሎ በለያቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ፣ በዛሬው ዕለት ተወያየ፡፡

የኢትዮጵያ ከተሞችን የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣ ወጪ ቆጣቢ የመኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ ያለውን ሁኔታ፣ በዲዛይን እና ኮንስትራክሽን ዕቃዎች ረገድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ማኔጅመንት ሲስተምን በተመለከተ፤ ምን ዓይነት ጥናት እና ምርምር ቢደረግ ለማኅበረሰቡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይችላል በሚሉት ጉዳዮች ላይ፤ ከሁለቱም ወገኖች ሐሳቦች ተሰንዝረው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፤ የምክር ቤቱ ኃላፊነት ሕግ ማውጣት፣ የተቋማትን ክትትል እና ቁጥጥር ማካሄድ፣ የውክልና እና የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን እንዳለበት አስረድተው፤ በሀገራችን የሚጠኑ ጥናቶች እና ምርምሮች ለይስሙላ ሳይሆን ታች ወርደው የሕብረተሰቡን መሠረታዊ ጥያቄ ሊመልሱ እና ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሰብሳቢዋ አክለውም፤ በጋራ ለመሥራት ጥሪ ተደርጎላቸው ለመጡት ምሁራን ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፣ የሕብረተሰቡን ችግሮች በጥናት እና ምርምር ለይቶ በጋራ ተቀራርቦ የመሥራቱ ነገር ከዚህ በፊት እንዳልተለመደ አስረድተዋል። አሁን ግን ለተከበሩ አፈ-ጉባዔ ለአቶ ታገሠ ጫፎ ጉዳዩን በማስረዳት ይሁንታ ከተገኘ በኋላ፤ ከምሁራን ጋር ተወያይቶ በቅንጅት ለመሥራት ቋሚ ኮሚቴው መነሳሳቱን አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም ሰብሳቢዋ የዩኒቨርስቲ ምሁራን ኮሚቴውን ለማገዝ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው፤ ተጨባጭ እንዲሁም ችግር ፈቺ መረጃዎችን ብቻ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የሚያመጡት የጥናት እና ምርምር ግኝቶችም ተግባራዊ እንደሚሆኑ፤ በኮሚቴው ስም ቃል ገብተዋል፡፡

ጥናት እና ምርምር ሲያካሂዱ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በደብዳቤ እንደሚያሳውቋቸው ሰብሳቢዋ አስጨብጠው፤ በሥራቸው ምንም ዓይነት ዕንቅፋት እንዳይደርስባቸው ኮሚቴው ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡

የሚያመጧቸው ግኝቶች ተፈጻሚነታቸው እንደሚረጋገጥ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ የጠቆሙት ወይዘሮ ሸዊት፤ አስፈጻሚ አካላትም ፖሊሲዎችን እና ሕጎችን እንደገና ማየት ከፈለጉም አጋዥ ይሆናቸዋል ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ ሙያዊ ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምሁራን ምክር ቤቱን ለማዘመን የሚችል የካበተ ሳይንሳዊ ዕውቀት አላቸው ብለዋል። የሀገራችንን ዕድገት ሊያፋጥኑ እና የሕዝብን ጥቅም ሊያስከብሩ በሚችሉ ጉዳዮችን በምርምር በመፍታት፤ ቀጣይነት ባለው መንገድ እየተጋገዝን እንሠራለን ብለዋል፡፡

የከተሞችን የመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሠራሮችን በአግባቡ መፍትሔ ለመስጠት፤ ጥናት እና ምርምር በማድረግ፣ ከምሁራን ጋር ተባብረን መሥራት አለብን ብለዋል - ዶ/ር ሄኖክ፡፡

ከሁለቱም ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ምሁራን ቋሚ ኮሚቴው ከላይ ባነሳቸው ችግር ፈቺ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የከተማ ምኅንድስና እና ልማት ኮሌጅ ዲን ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፤ ቋሚ ኮሚቴው ለጋራ ሥራ ስለጋበዘን እናመሰግናለን ብለዋል። ችግሮችን በጥናት እና ምርምር ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ርብርብም አድንቀዋል፡፡

ቀጣይ በጋራ እንደሚሠሩ እና የመፍትሔው አካል እንደሚሆኑም ተናግረው፤ አዋጆች እና ፖሊሲዎች በጥናት እና ምርምር ሲፈተሹ የሕዝብን ችግር እንደሚፈቱ አስገንዝበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የሥነ-ሕንጻ ዲዛይን ዳይሬክተር ሕያው ተፈራ (ዶ/ር ) ደግሞ፤ ጥናት እና ምርምር ሁሌ ቢደረግም ብዙም እየተተገበረ አለመሆኑን አስረድተዋል። ለአብነትም ከ11 ጥናት እና ምርምሮች ወደ ተግባር የሚቀየሩት 2ቱ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ከኮሚቴው ጋር በማኅበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ተጋግዘው ለመሥራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የከተማ መስተዳድሮች የምርምር ፈንድ ስለሌላቸው ጥናት እና ምርምሮችን ከሌላ ቦታ ገልብጠው እንደሚጠቀሙም አያይዘው አስረድተዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው