ቋሚ ኮሚቴው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን የ9 ወራት አፈጻጸም ገመገመ

(ዜና ፓርላማ)፣ ግንቦት 6/2013 ዓ/ም፤ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2013 በጀት ዓመት የ9 ወር እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

ሚኒስቴር መስሪ ቤቱ በክልሎች ለከተሞች መሰረተ ልማት አቅርቦት ድጎማ 5.9 ቢሊዮን ብር አቅዶ 5.2 ቢሊዮን ብር እንዳስተላለፈና የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ስራ በተመለከተ በትግበራ ላይ ያሉ የሶስት የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ስታንዳርዶችን ለመከለስ አቅዶ ማከናወኑን ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ቀደም ለ20/80 እና 40/80 ቤቶች ግንባታ ከቦንድ ውጭ ከተደረገው 7.65 ቢሊዮን ብር ተመላሽ ለማድረግ አቅዶ 6.25 ቢሊዮን ብር መኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳስመለሰ እና የመንግስት ቤቶችን አጠቃቀም ለማሻሻል እንዲሁም ሁሉንም የመንግስት ቤቶች በየዓመቱ ያሉበትን ሁኔታ በማጤን የውል እድሳት ለማድረግ ባታቀደው መሰረት የእቅዱን 81.74% ማከናወን እንደቻለም ኮሚቴው በጥንካሬ ገምግሟል፡፡

የከተማ ልማት ኮንስትራክሽና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የቢሮ ችግርን ለመፍታት ታስቦ ግንባታቸው የተጀመሩ የፌደራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ አፈጻጸም ሲገመገም የአብዛኛዎቹ  አፈጻጸም  ከዕቅዱ በታች ስለሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  ልዩ ትኩረት በማድረግ በቅንጅት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ዘመናዊ የማድረግና የአረንጓዴ ልማት ውበት ስራዎች የማጠናር ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ሰብሳበው የተከበሩ ወ/ሮ አገሬ ምናለ ከተሞች አሁን ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ በማካተት እና ተቋሙን በተለይ ከተማ ልማት ፖሊሲውን ለማሻሻል የተሄደበት ርቀት  ጥሩ እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ለልህቀት ማዕከሉ ማሰገንቢያ በየ ዓመቱ የሚበጀተው በጀት በዓመቱ መጨረሻ እየተመለሰ ስለሆነ  አዲስ አበባ ላይ መሬት ካልተገኘ ለሌሎችን ከተሞች አማራጭ በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባ ወ/ሮ አገሬ  ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት ያነሳቸውን እንደግብዓት በመውሰድ ቀጣይ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በ መስፍን አለሰው