ቋሚ ኮሚቴው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዘርፉን ሳይንሳዊና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሰራ አሳሰበ

(ዜና ፓርላማ) መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሙያውን ተፈላጊ፣ ሳይንሳዊና ውጤታማ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ይህን ያለው ሰሞኑን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ በወንጀል ምርመራ ቢሮና በሆስፒታል ባደረገው የመስክ ምልከታ ሲሆን የፖሊስን ሙያ ተፈላጊ፣ ተወዳዳሪና ሳይንሳዊ ማድረግ እንዲሁም በትምህርት እና ስልጠና ታግዞ በዕውቀቱ፣ በክህሎቱና በስብዕናው የዳበረ ፖሊስ ሠራዊት ማፍራት የግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

የወንጀል ምርመራ ቢሮዎችን በማዘመንና ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ በማድረግ፣ በሁሉም ክልሎች የምርመራ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈትና ከክልሎች ጋር ተናብቦ በመስራት በሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለይም ተጠርጣሪዎችን በመመርመር ሂደት የተከናወኑ ተግባራት የኮሚሽኑ አሰራር እየተሻሻለ መምጣቱን እንደሚያሳይ ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

ተቋሙ የ74 ዓመት ታሪክ ያለውን የፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳደጉ፤ አለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር ለሠራዊቱ ከዲፕሎማ እስከ ፒኤች ዲ የትምህርት ዕድል ማመቻቸቱና የፖሊስ ማዕረግ አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት ያደረገ መሆኑ ዘርፉን ለማዘመን የሠጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል ቋሚ ኮሚቴው፡፡

ኮሚሽኑ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የጀመረውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናከር እንዳለበት የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ከወንጀል ምርመራ ስራ አኳያ ከአቃቢ ህግ ጋር በሚሰሩ ስራዎች የአሰራር ክፍተት ስላለባቸው በርካታ መዝገቦች ወደ ፖሊስ እየተመለሱ እና ዜጎች እየተጉላሉ በመሆኑ ችግሮቹ መፈታት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በፖሊስ ሆስፒታል ጉብኝት ወቅት፣ የመድሃኒት አቅርቦት እና የህክምና መገልገያ መሰሪያዎች እጥረት፣ የሲቲ-ስካንና ኤም አርአይ ማሽኖች ግዥ መጓተት፣ የፎረንሲክና የቴክኒክ ባለሙያ እጥረት መኖሩን የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው ሆስፒታሉ ካለው አገራዊ ጠቀሜታ አኳያ ታይቶ ግብአት ሊሟላለት ይገባል በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት ፖሊስ ኮሚሽኑና የማዕቀፎቻቸው የስራ እንቅስቃሴ ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን የተገልጋይን እርካታ የበለጠ ለማሳደግ እንዲሁም ተቋሙን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፖሊስ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም እና የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተባባሰ በመምጣቱ ሰራዊቱና ቤተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንደ ህግ መቀመጥ እንዳለበትም አክለው ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ሌሎች አመራሮች የምርመራ ስራውን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግና ቀልጣፋ የፍትህ ስርዓት ለማስፈን የሚያግዙ ግብአቶችን ለማሟላት እንዲሁም የአባላት ጥቅማ ጥቅም ለማስከበር የተደረገ ጥረት ቢኖርም ለተፈፃሚነቱ የቋሚ ኮሜቴውን እገዛ በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡

አክለውም በህዝብ ዘንድ ታማኝ ተቋም ለመገንባት የሁሉም ክልሎች ተቋማትና አጋር አካላት መተባባርና ስራዎችን ወደ አንድ ቋት ማምጣት እንደሚገባ ተናግረው ለውጡ ከመጣ ጀምሮ አመራሩና አባላቱ ችግር በተፈጠረበት አካባቢ በመንቀሳቀስ ተጠርጣሪን ፍርድ ቤት ማቅረብ ስራው እንዳለ ሆኖ ከአቃቢ ህግ ጋር ወንጀል የመመርመር ስራው ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የገለፁት፡፡

በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 74 ዓመታት በፖሊስ ትምህርትና ስልጠና ፋና ወጊ ሆኖ የሀገሪቱን የፖሊስ ተቋም አቅም ሲገነባ የቆየ እና እየገነባ ያለ ተቋም እንደሆነ አስታውሰው ተቋሙ በአፍሪቃ በፖሊስ ትምህርትና ስልጠና የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

በአትጠገብ ቸሬ