(ዜና ፓርላማ)፣ የካቲት 26፣ 2013 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በግጭቶች ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮች  በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አብዱላና ሀሙ ገልፀዋል፡፡

ሰብሳቢው ይህንን የገለጹት ኮሚቴው ከትግራይ ክልል ውጭ በመተከል እና ሌሎች አካባቢዎች  ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን ተመልክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን የማሰልጠን እና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበር ከሕብረተሰቡ እና ከመተከል ኮማንድ ፖስት መረዳታቸውን ነው አቶ አብዱላሂ በመግለጫቸው ያብራሩት፡፡    

የተፈጠረው ግጭት የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ረዘም ያለ ዝግጅት የተደረገበት እና በኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ ሌላ አጀንዳ የነበራቸው አካላት “ክልሉ ሊፈርስ ነው ልትወረሩ ነው፤ ታጠቁ፤ ተዘጋጁ፤”  እያሉ ይቀሰቅሱ እንደነበር ሰብሳቢው አክለው ጠቅሰዋል፡፡

በአብዛኛው ወረዳዎች የሸሹ ታጣቂዎች የተመለሱ መሆኑን እና 3 ሺ የሚሆኑ ታጣቂዎች ደግሞ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ እጃቸውን መስጠታቸውን እና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የተደረጉ መሆኑንም አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡

በመተከል እና አካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ68 ሺህ በላይ የሚሆን የጉሙዝ ማኅበረሰብ ሸሸቶበት ከነበረው ጫካ እንደተመለሰም ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሚሊሻዎችን በመመልመልና በማሰልጠን የዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ አብዱላሂ ጠቅሰዋል፡፡

የጥፋቱ አካል የነበሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን ከቦታቸው በማንሳት ለሕግ የማቅረብ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ከኮማንድ ፖስቱ መረዳታቸውን አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ከተለያዩ የአካባቢው የሕብረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ግጭቱ   የሕዝብ ለሕዝብ እንዳልሆነና ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት የፈጠሩት ግጭት መሆኑን  መረዳታቸውን  አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት  ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በተጠለሉበት የተለያዩ ቦታዎች የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ነው ሰብሳቢው የተናገሩት ፡፡

የሰብዓዊ ድጋፉ ባልተቆራረጠ መልኩ እንዲከናወን የፌደራል እና የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ-አመራር ኮሚሽ ጋር በጋራ የሚሰራ የቴክኒክ ኮሚቴ ቡድን በማዋቀር እየተሰራ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍ ከማለቱ የተነሳ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ የማይደርስበት ሁኔታ መኖሩንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 125 ሺህ እንደሆነ ነው አቶ አብዱላሂ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡

በቂ የሰብአዊ ድጋፉ ለተፈናቃዮች እንዲደርስ መንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አቶ አብዱላሂ ጥሪ አቅርበው፣ መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቦታቸው የመመለስ፣ የስነ-ልቦና ግንባታ ስራዎችን መስራት እና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ  ስራ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡