(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 23፣ 2014፤ ሐዋሳ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ባደረገው የመስክ ምልከታ፣ በመዋቅር ጥያቄ ተንተርሰው የሚነሱ ግጭቶችን መከላከል እንደሚገባ አመላክቷል፡፡

በመዋቅር ጥያቄ ሰበብ ግጭቶች ተከስተው የሰው ሕይወት መጥፋትም ሆነ ንብረት ሊወድም እንደማይገባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አንስተው፤ ጥያቄዎቹ ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት መከላከል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

"ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ እንደ ሀገር የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀጠል፤ ዜጎች በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና በሚፈልጉት አከባቢ ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸውን ማስጠበቅ አለበት። የሕዝቦችን ሰብዓዊ መብት በማስከበር የተሻለች ኢትዮጵያ መፍጠር ያስፈልጋል" ቋሚ ኮሚቴው ከጽሕፈት ቤቱ ጋር ባደረገው ውይይት እንዳመለከተው፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ሥራዎቹን ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት ያሳሰበው ቋሚ ኮሚቴው፤ ከዚህ ቀደም በሥራ የቀመራቸውን ተሞክሮዎች ዐቅቦ እና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት አባላቱ አስታውሰዋል፡፡

የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር እና ለማረጋገጥ፤ የክልል መንግስታት እና መላው ሕብረተሰብ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር አብሮ በመቆም፣ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አባላቱ ጠቁመዋል፡፡

ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ማረሚያዎች፤ ችግር ፈቺ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን ተከትሎ፣ የዜጎችን መብት ከማስጠበቅ ረገድ በልዩ ሁኔታ ሊሠራ ይገባል ብለዋል - አባላቱ፡፡

የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ኢያሱ በሳላ፤ ዜጎች የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል አስተምህሮ እንዲኖር እና በሥርዓተ-ትምህርት እንዲካተት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እንዲቀየሩ መክረዋል። ለዚህ ዓላማ ዕውን መሆን ከሚያግዙ የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

የሐዋሳ ቅርንጨፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ክልሎችን በማካተት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውሰዋል። የመዋቅር ጥያቄን በሚመለከት በሚነሱ ግጭቶች በርካታ የሰው ሕይወት እና ንብረት እየወደመ በመሆኑ፤ በተደጋጋሚ በዚህ ጥያቄ ሰው የሚሞት ከሆነ ይህንን ጉዳይ የሚመልስ የመንግስት አካል ሊኖር ይገባል ብለዋል። የመዋቅር እና መሰል የማንነት ጥያቄዎች አሳሳቢ ሆነዋል ያሉት ኃላፊው፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሁሉንም የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የክልል መንግስታትም ሊያግዟቸው እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

አክለውም፤ ለጉዳዩ ተጋላጭ የሆኑ አከባቢዎችን እና የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፤ ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለእናቶች፤ ኮሚሽኑ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በ ለምለም ብዙነህ