(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 30፣ 2014 ዓ.ም.፤ በምክር ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት በአፈጻጸም ሂደት የታዩ መልካም ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አፈ-ጉባዔው አሳሰቡ፡፡

አፈ-ጉባዔው ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤቱን የ2014 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት ነው።

የምክር ቤቱን የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ያቀረቡት ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ አዲሱ 6ኛው ዙር የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህገ-መንግስታዊ ሀላፊነቱ ለመወጣት የሚያስችሉ 11 ቋሚ ኮሚቴዎችን እና የምክር ቤቱን አማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች በማደራጀት፣ የስራ ማስጀመሪያ ኦሬንቴሽን እና ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠት እንዲሁም የአምስት አመት መሪ ዕቅድ (2013-2017) በማዘጋጀት ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ስራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

በበጀት አመቱም ምክር ቤቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተዋፅኦዎችን ሊያበረክቱ የሚችሉ 17 ረቂቅ አዋጆችን ማጽደቁን፣ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በአካል በመገኘት ማብራሪያና ምላሽ እንዲሰጡ ማደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም አስፈጻሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ለምክር ቤቱ በቀጥታ በማቅረብ የዕቅድ አፈጻፀማቸውን በሚመለከት ከህዝብ፣ ከአባላት እና ከቋሚ ኮሚቴዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የየተቋሙ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ነው የገለጹት፡፡

አያይዘውም የኦዲት ግኝት የታየባቸው መ/ቤቶችም በግኝቶቻቸው ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱም ም/ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

አክለውም ኮሚቴዎች በግብርና፣ በፕሮጀክቶች አፈጻፀም፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋ ዙሪያ በከተማና በገጠር ውጤታማ መስክ ምልከታ ማድረጋቸውም ተናግረዋል፡፡

አባላት ወደመረጣቸው ክልሎች በመሄድ መራጩ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ይዘው በመምጣት በምክር ቤቱ በኩል ለአስፈፃሚ ተቋማት ተደራሽ በማድረግ ተቋማቱ ምላሽ እና እርምጃ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

በሁለትዮሽ እና በባለ ብዙ ዘርፍ የግንኙነት መድረኮች የተከበሩ አፈ-ጉባኤው በመገኘት እና እንደአሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ላሉ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እና አቋም በማስረዳት ፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲን የማጠናከር ስራ መሰራቱንም ነው ያመላከቱት።

ምክር ቤቱ ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ ማድረጉም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ሁሉም የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ አለመሆናቸው፣ አልፎ አልፎም ቢሆን የምክር ቤት አባላት በመደበኛ ስብሰባ ላይ በተሟላ ደረጃ አለመገኘትና ሠዓት አለማክበር፣ የተሟላ ተሽከርካሪዎች፣ ጠንካራ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የሞያተኛ ጥንቅር አለመኖር፣ የሚዲያ ስራ በሚፈልገው ጥራትና ፍጥነት ለህዝቡ ተደራሽ ያለመሆንን በእጥረት አንስተዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ሀገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ም/ቤቱ ያከናወናቸው ተግባራት በጥንካሬ እንደሚታዩ ተነስቷል፡፡

በሌላ በኩል የምክር ቤት አባላትን እና የህዝብን ጥያቄን በመመለስ ረገድ ችግር ያለባቸው ተቋማት በአግባቡ መታየት እንዳለባቸው፣ ለጠቅላይ ሚንስትሩም ሆነ ለሌሎች ሚንስትሮች ጥያቄዎችን ለሚያቀርቡ አባላት እኩል ዕድል ያለመስጠት፣ ስብሰባዎች አሰልቺ እንዳይሆኑ የሚደጋገሙ ሀሳቦችን ማስቀረት እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ በሰጡት ማጠቃለያ በቀረበው አስተያየት መሰረት በቀጣይ በጀት ዓመት በአግባቡ መታየት ያለባቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች በአግባቡ እንደሚታዩና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ካሉም ዳግመኛ ዕድል በመስጠት ተገቢውን ማብራሪያ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የምክር አባላት የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች በፍትሀዊነት ለማስተናገድ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው፣ ዕድሉን ሌሎችም እንዲያገኙ አባላት ጥያቄአቸውን መመጠንና ማሳጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም በአፈጻጸም ሂደት የታዩ መልካም ጅምሮች ተጠናክረው የሚቀጥሉ እና እጥረቶችና ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ለቀጣዩ ዕቅድ እንደ ግብዓት ተወስደው ማሻሻያ እንደሚደረግባቸውም ነው ያብራሩት፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ