(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 22፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዳማ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተከማችተው የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ለፀሀይ እየተጋለጡ ስለሆነ፣ በአስቸኳይ ሊወገዱ አሊያም መጠለያ ሊዘጋጅላቸው እንደሚገባ አሳሰበ፡፡

ኮሚቴው ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው፤ የአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ2013 እና በ2014 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት መሠረት እየወሰደ ያለውን የዕርምት እርምጃ ለማጣራት ባደረገው የመስክ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

በክዋኔ ኦዲት ግኝትነት የተመዘገቡት የሰው ኃይል አለመሟላት፣ የሕገ-ወጥ ንግድ ዕቃ መረጃ አያያዝ ውስንነት መኖር፣ የሕገ-ወጥ ንግድን አስከፊነት በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አለመስጠት፣ ለኮንትሮባንድ ጠቋሚዎች ተገቢውን የወረታ ክፍያ አለመፈጸም፣ በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የኦፕሬሽን ሥራ አለማከናወን እና በዕቃዎች አወጋገድ ላይ መዘግየት መታየቱ፤ በዋናነት የሚጠቀሱ የቅርንጫፉ የቀድሞ ዕጥረቶች ናቸው፡፡

የኮሚቴው አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ደረጄ ደበላ፤ ቀሪ ሥራዎች እያሉትም ቢሆን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የክዋኔ ኦዲት ግኝትን ለማረም እየወሰደ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ቅርንጫፉ በተሻለ ሁኔታ የሰው ኃይል ማሟላቱን፣ ለጠቋሚዎች ውዝፍ የወረታ ክፍያ መፈጸሙን፣ ከፀጥታ አካላት ጋር የፈጠረውን ቅንጅታዊ አሠራር በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት፣ በአንዳንድ ቦታዎች የኮንትሮባንድ ንግድ መኖሩ አሁንም የሚቀር ሥራ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

እንደዚሁም የሀገር ሀብት የሆኑት በርካታ ተሽከርካሪዎች ያለመጠለያ ለፀሀይ እና ለዝናብ የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚወገዱበትን፣ አለበለዚያ መጠለያ የሚዘጋጅበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ባልቻ፤ በመዋቅሩ መሠረት የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ መሠራቱን፣ የሚያዙ ዕቃዎች በአግባቡ እየተመዘገቡ መሆኑን፣ የሕገ-ወጥ ንግድን አስከፊነት በተመለከተ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን፣ ለኮንትሮባንድ ጠቋሚዎች ከጥቂቶች በስተቀር የወረታ ክፍያ መፈጸሙን፣ በደፈጣ፣ በበረራ እና በኦፕሬሽን በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን፣ ተሽከርካሪን ጨምሮ የተያዙ ዕቃዎች በስጦታ፣ በሺያጭ እና በማውደም እንደሚወገዱ አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሮጌ ተሽከርካሪዎች ከውጪ እንዳይገቡ የሚያበረታታው አዋጅ ከወጣ በኋላ የገቡ 162 ገደማ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ባለቤቶቹ አዲሱን ቀረጥ ከፍለው ሊወስዱ ባለመቻላቸው ተከማችተው እንደሚገኙ ገልጸው፤ የተተወ ንብረት በሚል ቅርንጫፉ ለሺያጭ ለጨረታ ቢያወጣቸውም ከክልሉ ፍርድ ቤት ማገጃ በማምጣታቸው ጨረታው መቋረጡን አስረድተዋል፡፡

አክለውም ለተሽከርካሪዎቹ መጠለያ ለማሠራት 1 ቢሊየን ብር በመገመቱ መቸገራቸውን ለኮሚቴው አሳውቀዋል፡፡

ኮሚቴው በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የ2013 እና የ2014 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝትን መነሻ በማድረግ በኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገውን የማጣራት ስራ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በቅርቡም ለኮሚሽኑ የማጠቃለያ ግብረ-መልስ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ