በካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት ተካሄደ፡፡

ዜና ፓርላማ መጋት 23፣ 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ በተመራላቸው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲ ሪፐብሊክ የካፒታል ገበያ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱም የአዋጁ አስፈላጊነትና ፋይዳ? አዋጁ ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ግሽበት ተጋላጭ አያደርግም ወይ? ኢኮኖሚውን የውጭ ባለሃብቶች እንዳይቆጣጠሩትና አገሪቱ ወደ ማትወጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ምን ታስቧል? የሚሉ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስተው በተጠሪ ተቋማት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በምላሻቸው እንዳሉት ቀደም ሲል የነበረው አሰራርም ሆነ አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ የሚያሳትፍና የውጭ አገር ዜጎችን ተጠቃሚ የማያደርግ ስለነበር ይህን አሰራር ለማሻሻልና የውጭ አገር ዜጎችን በካፒታል ገበያው ተሳታፊ ለማድረግ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ በንቃት እንዲሳታፉ ከመጋበዙም በላይ አክሲዮን እና ቦንድ የመሳሰሉ የሰነድ ገበያን በመፍጠር የህብረተሰቡን የቁጠባ ልምድ እና አቅምን በማሳደግ የተጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሳደግ የካፒታል ገበያ አዋጅ ተቀዳሚ ተግባር እንደሆነም ነው የባንኩ ገዥ የተናገሩት፡፡

የባንኩ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አክለውም ለካፒታል ገበያው ውጤታማነት ከፍተኛ የባለሃብት ተሳትፎ፣ የካፒታል መሰረተ ልማት መሟላት እና ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ ጠንካራ አመራር የሚያስፈልግ በመሆኑ ለጊዜው እውቀቱ ካላቸው ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ተወላጆች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡        

በብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ መለሰ ምንአለ በበኩላቸው የውጭ ባለሃብቶችን በካፒታል ገበያ ተሳታፊ በሚደረግበት ጊዜ ከዚህ ቀደም በባንኩ የወጣው ክልከላ እንደተጠበቀ ሆኖ በፋይናንስ ዘርፍ በማማከር፣ በማገናኘትና መሰል አገልግሎቶች ላይ ተሳታፊ የሚያደርግ በመሆኑ ኢኮኖሚውን ከመደገፍም በላይ ካፒታል ገበያ ጥቅሙ በርካታ ኢንቨስትመንት ለረጅም ዓመታት እንዲኖር በማድረግና የረጅም ዓመት የብድር አቅምና እድልን የሚፈጥር መሆኑን በምላሻቸው አብራርተዋል፡፡

አማካሪው አክለውም አዋጁ አገራት ከፍተኛ በሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በሚገቡበት ወቅትም መንግስት ከካፒታል ገበያው ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ኢኮኖሚያቸውን የሚደግፉበት ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ ይህ አዋጅ የሌሎች አገራት ተሞክሮ የተወሰደበትና ጥናት የተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በእያሱ ማቴዎስ