(ዜና ፓርላማ)፣ መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም፤ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ብዛት መሰረት በማድረግ መንግስት ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ነው ፕሬዚዳንቷ ገለጻውን ያቀረቡት።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ በ2014 በጀት ዓመት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች ከዕቅዱ አኳያ ተስፋ ሰጪ ውጤት የተገኙበት ቢሆንም፣ ግጭት እና መፈናቀል ካልተሻገርናቸው ችግሮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም ፕሬዚዳንቷ አብራርተዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ጥሎት ባለፈው ጠባሳ፣ ጦርነት በፈጠረው የኢኮኖሚ ውድመት እንዲሁም ጎርፍና ድርቅ ባሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖ ኢኮኖሚው ሳያሽቆለቁል ይልቁንም እድገት ማስመዝገብ መቻሉ ትልቅ ውጤት እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡ 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሰፊ ሥራ ከተሠራባቸው ዘርፎች መካከል አንድ ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞች የተሳተፉበት የማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፉ አንዱ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል። 

በተለይም በጦርነት የወደሙ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ሕዝቡን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወሰዳቸው እርምጃዎች ትልቅ ውጤት እንዳስገኙ ተናግረዋል። 

በ2014 በጀት ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የላቀ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ ይኸውም ለአቅመ ደካሞች ቤት በመሥራት፣ አዳዲስ እና ነባር ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና በመጠገን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል። 

በማኅበራዊ ዘርፉ የነበሩ ጠንካራ ሥራዎችን በማስቀጠል የነበሩ ድክመቶችን በማረም በ2015 የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።

በ አበባው ዮሴፍ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ