(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 11፣ 2014 ዓ.ም.፤ ጅግጅጋ፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እና አካባቢዋ በዛሬው ዕለት በሚደረገው እንቅስቃሴ፤ አረንጓዴውን አሻራ ከማሳረፍ ባሻገር፤ ሠላሳ ቤቶች ይታደሳሉ፣ ይጠገናሉ።

ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የተሠራጨው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ የሚታደሱት መኖሪያዎች የዓቅመ-ደካማ ዜጎች ቤቶች ይሆናሉ።

የተጠቀሱትን ተግባራት ደግሞ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጎን በመሆን፤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋራ እንደሚያከናውኑ ይኼው መረጃ ጨምሮ ያስረዳል።

እነዚሁ ተቋማት ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ የገንዘብ መዋጮ ከማበርከታቸው በላይ፤ የሰው ኃይላቸው በአካል ተገኝቶ እንዲሳተፍ እንዳደረጉም መገንዘብ ተችሏል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሕዝብ ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ሕዝባዊ ወገንተኝነት በተግባር ሲያረጋግጥ የቆየ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

ምንም እንኳን ዋና ሥራው እና ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮው ሕግ ማውጣት እና የጸደቁ ሕጎች ደግሞ ምን ያህል መሬት እንደነኩ መከታተል እና ማረጋገጥ ቢሆንም፤ ለአብነት ዜጎች በጎርፍ አደጋ ሲጠቁ፣ የአንበጣ መንጋ እና ድርቅ አደጋ ሲያስከትሉ ከሕዝብ ጎን በመቆም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በተደጋጋሚ ማስመስከሩ አይዘነጋም።

በ አሥራት አዲሱ