(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 12፣ 2014 ዓ.ም.፤ ጅግጅጋ፤ በክረምት ወራት የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት እና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሕዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ የሚፈጸሙ ሥራዎች፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓይነተኛ ባሕርያት መሆናቸው ተገለጸ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ይህንን የገለጹት፤ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እና አካባቢዋ የተከናወነውን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር እና የዓቅመ-ደካማ ዜጎችን መኖሪያዎች የማደስ ሥራ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

የምክር ቤቱን እና የስድስት ተጠሪ ተቋማትን የሥራ ኃላፊዎች መርተው በዚህ እንቅስቃሴ የተሳተፉት የተከበሩ አፈ-ጉባዔ፤ ምክር ቤቱ እነዚህን ተግባራት በራሱ ተነሳሽነት እና ሌሎች ተጠሪ ተቋማትን ጭምር በማሳተፍ የሚያከናውነው፣ በተላበሰው ሕዝባዊ ወገንተኝነት መንስዔ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር እየተካሄደ ያለው አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ መርኃ-ግብር፤ ድርቅን በመቆጣጠር፣ ዘላቂ ልማትን እና ብልጽግናን ለማሳካት የጎላ ፋይዳ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ አህጉራዊ አጀንዳውን ጭምር ለማሳካት በሚያበቃ ደረጃ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ብለዋል።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ፣ ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች፤ በዚሁ በጅግጅጋ ከተማ እና በአካባቢዋ የክረምት የበጎ ፈቃድ እና የቤት ዕድሳት ሥራዎች ተሳትፈዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ ደግሞ፤ የተራቆቱ አከባቢዎችን መልሶ በደን ለመሸፈን እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በረሃማነትን ከመከላከል ባሻገር ለምግብነት የሚያገለግሉ ፍራፍሬዎች እና ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸው የዛፍ ዓይነቶች እንደሚተኮርባቸውም አመላክተዋል።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ "በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ነድፋ፣ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የኃይል አቅርቦትን ለመሸፈን ጥረት እያደረገች ትገኛለች" ብለዋል። የአረንጓዴ አሻራው ደግሞ ግድቦችን ከደለል በመጠበቅ፣ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመቋቋም ባሻገር በሁሉም አካባቢዎች ችግኞችን መትከሉ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከማገዙ በላይ ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ለመከላከል አስተዋጽዖ እንዳበረከተ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፤ የመሬት መሸርሸርን ለመከላከል እና የውኃ አካላት እንዳይደርቁ ከማድረግ ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሙቀት እና ድርቅ ለመቀነስ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ በበኩላቸው፤ የችግኝ ተከላ ተግባር ለሶማሌ ክልል የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር 1 ሚሊዮን 5 መቶ ሺህ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመው፤ ይህም የ2063 የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ አካል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በተከበሩ ታገሠ ጫፎ የተመራው የከፍተኛ አመራር ቡድን ለክልላቸው ትኩረት በመስጠቱ፤ በክልሉ ሕዝብ እና በራሳቸው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚዲያ ክፍልም በስፍራው ተገኝቶ፤ በምክር ቤቱ አነሳሽነት የተከናወኑትን የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራትን እንዲሁም ሠላሳ የዓቅመ-ደካማ ቤቶችን የማደስ ሥራዎች እየተከታተለ ሲያስነብባችሁ መቆየቱ ይታወቃል።

በ አሥራት አዲሱ