(ዜና ፓርላማ)፤ መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ ባለፈው በጀት ዓመት ተግዳሮቶች ቢኖሩም በፖለቲካው እና በዲፕሎማሲው መስክ ስኬቶች መመዝገባቸውን ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ፤ የ2015 በጀት ዓመት የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀምጠዋል፡፡ 

ክብርት ፕሬዚዳንቷ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ንግግራቸው ባለፈው የ2014 በጀት ዓመት ሀገሪቱ በበጎም ሆነ በበጎም ባልሆነ የሚታወሱ ትልልቅ ሁነቶችን ማስተናገዷን ገልጸዋል፡፡ 

በሀገሪቱ የተካሄደው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ለሀገሪቱ የአዲስ ምዕራፍ ሆኖ ማለፉን በስኬት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ሕዝቡን በሀዘንና ጭንቀት ውስጥ የከተቱ ተግዳሮቶች መከሰታቸውንም አብራርተዋል፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶች እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በንጹሀን ዜጎች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ በአሉታዊ ጎን የሚታወሱና በዚህ ሳቢያ የተፈጠሩ ግጭቶችና መፈናቀሎችንም ሀገሪቱ ያልተሻገረቻቸው ችግሮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት ለሰላም ቁርጠኛ በመሆኑ ግጭት ጨርሶ እንዲያበቃ ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ግጭቱ እንዲቆም በተደጋጋሚ መጣሩን አስታውሰው፤ አሁንም መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሰላም ጥሪውን የሚያቀርብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም አካታች የሆነ የፖለቲካ ምህዳርን ለመፍጠር እንዲሁም በሁሉም ሀገራዊ ሀሳቦች ላይ ምክክር እንዲደረግና ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከህብረተሰቡ የተውጣጡና ብቃት ያላቸው አባላት የተካተቱበት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በዲፕሎማሲው ረገድም ሀገሪቱ ቁርጠኝነቷን በማሳየት በአፍሪካና በቀጠናው በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውስጥም በአፍሪካ ህብረት በኩል ለሰላም እየተደረገ ያለውን ጥረት አንደኛው መሆኑና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል፡፡

በግብፅና በሱዳን ሀገራት መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የተጠናከረ ዲፕሎማሲ ስራ እንደሚሰራም ነው ባስቀመጡት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ያመላከቱት፡፡

በበጀት ዓመቱም ሀገሪቱን ሲፈትናት የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ የሁሉንም ጥረት እንደሚጠይቅም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡  

በ ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ 

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ