(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 26፣ 2014 ዓ.ም.፤ ጅግጅጋ፤ ከሶማሌ ክልል የተመረጡ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ ከክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ከክቡር ሙስጠፌ ሙሐመድ ጋር በመሆን ባካሄዱት ውይይት፣ የክልሉን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች በጋራ ለዩ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተወያዩት፤ ሰሞኑን የፌዴራሉ ፓርላማ እና የክልሉ ምክር ቤት አባላት በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ለክትትል እና ቁጥጥር ሥራ ተሰማርተው ባመጡት ግኝት ላይ ተመርኩዘው ነው።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባል የተከበሩ አቶ ከማል ሀሺ እንደገለጹት፤ ርሳቸው የተካተቱበት ጥምር የክትትል እና ቁጥጥር ቡድን በክልሉ ለተከሰተው ድርቅ መንግስት እየሰጠ ያለውን ምላሽ በአካል ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን፣ ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶችን እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎችንም ጎብኝቷል።

ይኼው የመስክ ምልከታ ቡድን የምልከታውን ሪፖርት አጠናቅሮ፤ በምልከታው የለያቸውን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች የቃኘ ግብረ-መልስ ለክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ለክቡር ሙስጠፌ ሙሐመድ አቅርቧል። ከርሳቸው ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላም፤ አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች፣ ወደፊት በጠንካራ ጎን መቀጠል ያለባቸውን ዘርፎች እንዲሁም መሻሻል ያለባቸውን ክንውኖች በተመለከተ፤ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር ክቡር ሙስጠፌ ሙሐመድ በሰጡት ማጠቃለያም፤ የሕዝብ እንደራሴዎች ከክልል ምክር ቤት አባላት ጋር በጥምረት ላካሄዱት የክትትል እና የቁጥጥር ስራ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል። መንግስት ለሕብረተሰቡ እየሰጠ ያለው አገልግሎት እየተሻሻለ እንዲሄድም፤ ከሶማሌ ክልል ከተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር፣ በቋሚነት የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡