(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 16፣ 2014 ዓ.ም.፤ ስልጤ፤ አብሮነትን ለማጎልበት መቻቻልን ማጠናከር እንደሚገባ የፓርላማ አባላት ገልፀዋል።

ከተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጡ የፓርላማ አባላት በደቡብ ክልል፣ ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ ተገኝተው፤ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ለማጎልበት መቻቻልን ማጠናከር እንደሚገባ ገለጹ።

አባላቱ ይህንን የገለጹት፤ በቅርቡ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ የዕምነት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር እየተካሄዱ ያሉ ተግባራትን፣ ሰሞኑን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ነው።

የፓርላማ አባላቱ ኢትዮጵያዊ የአብሮነት ዕሴትን ማጠናከር የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ በየትኛውም አካባቢዎች የሚነሱ የጽንፈኝነት ዕሳቤዎች የሀገርን ሕልውና ስለሚጎዱ፣ በዚህ ጎጂ ዝንባሌ ላይ አተኩሮ በመሥራት ማቀጨጭ እና ማስወገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አባላቱ በተለያዩ የስልጤ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ፤ ስልጤ ሰላማዊ እና የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት መሆኑን ማስተዋላቸውን ገልጸዋል።

ችግሩ ከተፈጠረ ማግስት ጀምሮ ክስተቱን በማውገዝ እና የተጎዱ ተቋማትን ለመገንባት ሕብረተሰቡ መዋጮ በመሰብሰብ ጭምር ያሳየው አብሮነት የሚደነቅ መሆኑንም አባላቱ ተናግረዋል።

በውይይት እና ምልከታ መርኃ-ግብሩ የተገኙ የኃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፤ ፓርላማው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ፣ ቦታው ድረስ በመምጣት እውነታውን ለመረዳት ላደረገው እንቅስቃሴ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ችግሩ በየትኛውም መመዘኛ ሰላም ወዳዱን የስልጤ ሕዝብ የማይወክል ነው ያሉት እነዚሁ አካላት፤ በሀገሪቱ ብጥብጥ እና ሁከት ለመቀስቀስ ያሰቡ አካላት እጅ ስላለበት ድርጊቱን ኮንነዋል።

ከዚህ በተቃራኒ የስልጤን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማጥላላት እና በሕዝቦች እና ዕምነቶች መካከል መተማመን እንዳይፈጠር የሚሠሩ አካላት ከተግባራቸው እንዲመለሱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በመደበኛ እና ማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን የሐሰት መረጃ እየነዙ የሚቀሰቅሱ አካላት ፈጣሪን ፈርተው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም የኃይማኖት አባቶቹ ጠይቀዋል።

የስልጤ ዞን ግብርና መምሪያ እና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙርሰል አማን በበኩላቸው፤ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ 145 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከድርጊቱ ጋር ተሳትፎ የሌላቸው አካላት ተለይተው እየተፈቱ ከመሆኑም በላይ፤ የተጎዱትን ተቋማት መልሶ ለመገንባት በሁሉም የስልጤ አካባቢዎች ገንዘብ እየተሰበሰበ በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ተገንብተው እንደሚጠናቀቁ ያላቸውን ተስፋ አብስረዋል።

በዚህ የሰላም ተልዕኮ መርኃ-ግብር የፓርላማ አባላት፣ የስልጤ ዞን የኃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ የስልጤ ዞን አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ሆነዋል።