(ዜና ፓርላማ)፤ ሐምሌ 1፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው አዲሱ የ2015 በጀት፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችል እና የፋይናንስ ዓቅም ያገናዘበ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው።

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ በበጀት ረቂቅ አዋጁ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ከተጋበዙ አስረጂ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። የዜጎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሕዝብ ይፋዊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት፤ በቂ ውይይት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

የ2015 ረቂቅ በጀት ዝግጅት ትኩረቱ፤ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ለማድረግ፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለተከሰቱት ተጨማሪ የወጪ ፍላጐቶች፣ ለሰብዓዊ እርዳታ፣ ለመልሶ ግንባታ እና የመከላከልን ዓቅም ለማጠናከር መሆኑን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለዕዳ ክፍያ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ በሀገሪቱ የመካከለኛ ዘመን የማክሮ-ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንዲጸድቅ የቀረበው የ2015 ጠቅላላ የወጪ በጀት ብር 786,610,053.114 ቢሊዮን ሲሆን፤ ከነዚህም ለፌዴራል መንግስት የመደበኛ ወጪ ብር 345,116,460,530 ቢሊዮን (44%)፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218,112,877,804 ቢሊዮን (28%) ሆኖ ተመድቧል።

በአብዛኛው ቀደም ሲል በዕቅድ ተይዘው በ2014 ዓ.ም. ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እና በጦርነቱ ምክኒያት የወደሙትን መሠረተ-ልማቶች እና አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት እንዲሁም መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ ትኩረት እንደተሰጠም ተናግረዋል፡፡

ክልላዊ መንግስታት፣ ድሬዳዋን እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የበጀት ድጋፍ ብር 209.38 ቢሊዮን (26%) የበጀት ድርሻ ያላቸው እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ብር 14 ቢሊዮን (2%) መሆኑንም አክለዋል፡፡

አያዘውም፤ በአሥር ዓመቱ የፍኖተ-ብልጽግና ዕቅድ መሠረት ከ2015 ዓ.ም. አጠቃላይ የፌዴራል መንግስት መደበኛ እና ካፒታል በጀት ወጪ በድምሩ 563.23 ቢሊዮን ከተመደበው ውስጥ፣ 37.6 በመቶ ትኩረት ለተሰጣቸው የድኅነት-ተኮር ፕሮግራሞች እንደሚውል አስረድተዋል። ለትምህርት፣ መንገድ፤ ግብርና፣ ውሃ፣ ጤና፣ የከተማ ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት፣ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ትርጉም ላላቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለኤክስፖርት እና ለከተማ ልማት ዘርፎች፣ እንዲሁም 22.36 በመቶ ለእዳ ክፍያ እና 14.91 በመቶ ለመከላከያ ከአጠቃላይ የፌዴራል በጀቱ ውስጥ ድርሻ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የ2015 ረቂቅ በጀት በ2014 ዓ.ም. ከጸደቀው በጀት እና ተጨማሪ በጀትን ጨምሮ ከጠቅላላ በጀት ጋር ሲነጻጸር የ111.94 ቢሊዮን ጭማሪ ወይም የ16.59 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የ2015 በጀት አመት የወጪ አሸፋፈንም ከፌዴራል መንግስት፣ ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች እና ከውጭ እርዳታ ብር 477.78 ቢሊዮን እንደሚሰበሰብ፣ ከዚህ ውስጥ ከሀገር ውስጥ ገቢ ብር 438.85 ቢሊዮን፣ በቀጥታ በጀት ድጋፍ ከሚገኝ መሰረታዊ አገልግሎት ከለላ እርዳታ ብር 7.66 ቢሊዮን እና ከፕሮጀክቶች እርዳታ ብር 31.27 ቢሊዮን እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የተመደበው የ2015 ዓ.ም. በጀት በቁጠባ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ምክር ቤቱ የተጠናከረ ክትትል ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የሀገሪቱ የ2015 ረቂቅ በጀት፣ በምክር ቤቱ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አዋጅ ቁጥር 1275/2014 ዓ.ም ሆኖ በ4 ድምጸ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁ ይታወሳል፡፡

በ ኃይለሚካኤል አረጋኸኝ