(ዜና ፓርላማ)፤ ጳጉሜን 1፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ፤ የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ እና የሕንድ ሪፐብሊክ አምባሳደሮችን በጽሕፈት ቤታቸው አነጋገሩ።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ሰሞኑን ከአምባሳደሮቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሁለቱ ሀገራት እና በኢትዮጵያ መካከል ስለሚኖረው ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉት ከእነዚሁ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ተወያይተዋል።

የተከበሩ ታገሠ ከሞዛምቢክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጋር ባካሄዱት ውይይት፤ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ተነጋግረዋል። ይህ ግንኙነትም ዳብሮ የጠነከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ወዳጅነት መመሥረት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም እንደዚሁ ሐሳቦችን ተለዋውጠዋል።

ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የቆየ ግንኙነታቸውን በማደስ እና በማጎልበት፤ በምጣኔ-ሀብቱ ዘርፍም የእርስ በርስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም፤ ሁለቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተግባብተዋል። በተጨማሪም፤ ሁለቱ ሀገራት ከራሳቸው በዘለለ አፍሪካ እንደ አህጉር በምጣኔ-ሀብት፣ በሰላም እና ፀጥታ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጠንክራ እንድትወጣ ማበርከት በሚችሉባቸው አስተዋጽዖዎች ረገድ ተነጋግረዋል።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ በተመሳሳይ ከሕንድ አምባሳደር ጋርም፤ በፓርላማ ለፓርላማ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል። በተለይ ታሪካዊውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ቀደም ሲል ከነበረበት ምጣኔ-ሀብታዊ የትስስር ደረጃ በላይ ለማራመድ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ፤ ሁለቱ ኃላፊዎች ሐሳቦችን ተቀያይረዋል።

የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ከሁለቱ አምባሳደሮች ጋር ያካሄዱት ውይይት፤ በዚህ መልኩ በቀና የትብብር እና የአብሮነት መንፈስ መጠናቀቁን ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በ አሥራት አዲሱ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/watch?v=cp_8F5TEeFE

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ